ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራትን ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ማገዝ ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራትን ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ማገዝ ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ፤የካቲት 28/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች በጥናትና ምርምር ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የአየር ንብረት ፎረም ለመመስረት ያለመ ውይይት እያደረገ ይገኛል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየተተገበሩ የሚገኙ መርሐ ግብሮችን ለማሳካት ዩኒቨርሲቲዎቹ ምርምሮችን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝም አንስተዋል።
መንግሥት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን መሰረት ያደረጉ ስራዎችን እየተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ልማት፣ የታዳሽ ኃይል አመራጭን መጠቀምና የአየር ብክለትን የመቀነስ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተለያዩ ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችን ቀርጾ እየተገበረ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግዳሮት ሆኖ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት በጥናትና ምርምር ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ እያደረገቻቸው ያሉትን ጥረቶች ለዓለም በማሳወቅ በኩል መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ፋይናንስ ለማፈላለግ የሚደረገውን ድርድር ማገዝ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲዎች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እየተሰሩ ያሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ወደተግባር እንዲገቡና ለፖሊሲ ግብዓትነት እንዲውሉ መትጋት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በዚህም ቀጣይነት ያለው ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።