በኢትዮጵያ እና ህንድ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እና ህንድ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር ይሰራል
አዲስ አበባ፤የካቲት 28/2017 (ኢዜአ)፦የህንድ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን (FICCI) በኢትዮጵያ እና ህንድ መካከል ያለውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰራ አስታወቀ።
በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሃ ሻውል፥ ከህንድ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሃርሻ ቫርዳሃን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ በፌዴሬሽኑ ስር የሚገኙ 35 ታዋቂ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል።
አምባሳደር ፍስሃ ስለ ኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም፣ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት የትኩረት መስኮች እና በዘርፉ ስላሉ እድሎች ገለጻ አድርገዋል።
አምባሳደሩ የህንድ ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስክ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ፌዴሬሽኑ የሀገራቱን የንግድ እና ኢንቨስትመንት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የህንድ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን እ.አ.አ በ1927 የተቋቋመ ግዙፍ የንግድ ተቋም ነው።
ተቀማጭነቱን በኒው ዴልሂ ያደረገው ምክር ቤቱ ከ250 ሺህ በላይ የመንግስት፣ የግሉ ዘርፍ ግዙፍ እና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን በአባልነት ይዟል።