ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት በዲጂታል ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ኢማኑኤል ምናሴ (ዶ/ር) በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።


 

ውይይቱ በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ትግበራ ላይ በትብብር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፥ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየሰራች ነው ብለዋል።

ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት መፋጠንና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እውን ማድረግ ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ በዲጂታል ኢኮኖሚው ላይ በትብብር በመስራት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እና ባለቤትነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል አመልክተዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማሸጋገር በሚያስችለው የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ላይ እምርታዊ እድገት ለማምጣት የሚያስችሉ የትብብር ስራዎችን በማጠናከር የዲጂታል ኢኮኖሚውን እድገት ለማሳካት እንደሚሰራ ተናግረዋል።


 

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ ሁሉን አቀፍ ስራ እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት (ITU) በኩል የሚወጡት የሀገራት የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽንስ ቴክኖሎጂ ደረጃ ፍትሃዊነት እና የሀገራትን ወቅታዊ ስራዎች ከግምት ውስጥ ያስገቡ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት (ITU) የአፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ኢማኑኤል ምናሴ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ የያዘችው ግብ እንዲሳካ ተቋማቸው በትብብር እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ህብረቱ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራን ለማሳለጥ እየተከናወኑ ላሉ ስራዎች ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።

በቀጣይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ስለሚወጡ መረጃዎች  ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም