ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የሥርዓተ ምግብ ፖሊሲን በመተግበር ለአፍሪካ ምሳሌ ሆናለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የሥርዓተ ምግብ ፖሊሲን በመተግበር ለአፍሪካ ምሳሌ ሆናለች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የተከተለችው ሀገር በቀል የግብርና እና የሥርዓተ ምግብ ፖሊሲ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።
በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የመጀመሪያው የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የስርዓተ ምግብ ከፍተኛ የመማማሪያ መድረክ ተጠናቋል።
ሚኒስትሩ በማጠቃለያው ላይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በግብርና እና በስርዓተ ምግብ ያከናወነቻቸውን ተግባራት በመድረኩ ከማሳየት ባለፈ ልምዷን አካፍላለች።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተከተለችው ሀገር በቀል የፖሊሲ ዕይታ ስኬት እያስመዘገበች መሆኗን ጠቅሰው፤ ይህም አፍሪካውያን ተመሳሳይ መንገድ እንዲከተሉ ትምህርት የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀብቶችን በማቀናጀት የምግብ ስርዓትና ደህንነትን ማሻሻል ላይ እያስመዘገበች ያለውን ስኬትም በተሞክሮነት ማጋራቷን ተናግረዋል።
ፈጠራ የታከለባቸው ኢኒሼቲቮች በመቅረጽ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው በመድረኩ የኢትዮጵያ በስንዴ ራስን የመቻል ስራ በተሞክሮ መቅረቡን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ በአለም ላይ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር መፍቻ መንገድ ቴክኖሎጂን ገበሬ ጋር በማድረስ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ ይፋ ማድረጓን ጠቁመው ይህም ወደ ትግበራ እየገባ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ተሞክሮ በጉልህ መነሳቱን ገልጸው ኢትዮጵያም በቀጣይ በሚኖሩ መድረኮች ልምዷን ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለች ብለዋል።
በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርናና ገጠር ልማት ዳይሬክተር ጎድፍሬይ ባሂግዋ በበኩላቸው በተለያዩ አገራት ያሉ ልምዶችን መለዋወጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በአህጉሪቱ በርካታ ሊካፈሉ የሚገባ ተሞክሮዎች መኖራቸውን ገልጸው የኢትዮጵያ በስንዴ ራስን መቻል ስራ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።