የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን አገልግሎቱን የሚያዘምኑ አሰራሮችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን አገልግሎቱን የሚያዘምኑ አሰራሮችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን አሰራሮቹን በማዘመን የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
ተቋሙ ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው የፈቃድ አሰጣጥና ዕድሳት አገልግሎቶችን በኦንላይን ማግኘት የሚችሉበትን ኢ-ሰርቪስ አገልግሎት ይፋ አድርጓል፡፡
ይህም አገልግሎትን የሚያሳልጥ፣ የተገልጋዮችን እንግልት የሚቀንስ፣ ጊዜና ገንዘብን የሚቆጥብ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ጌታቸው፤ ወደአገር ውስጥ የሚገቡና ከአገር የሚወጡ ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚደረጉ ቁጥጥሮችና ሌሎች አገልግሎቶችን የማዘመን ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የጨረራና ኒውክለር ቴክኖሎጂ አገልግሎትም የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጥራት አስተዳደር ስርዓትም ዓለም አቀፍ ተሞክሮን በመቀመር የተቀናጀ የአስተዳደር ስርዓት ተዘርግቶ እየተተገበረ ነው ብለዋል።
ባለስልጣኑ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶችን ቀልጣፋና ዘመናዊ የማድረግ ሥራን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።
ዛሬ ይፋ ይሆነው ኢ-ሰርቪስ ተገልጋዮች ካሉበት ሆነው የሚፈልጉትን አገልግሎት በኦንላይን ማግኘት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
አገልግሎቱ ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በተጨማሪ ደንበኞች የአገልግሎት ማመልከቻቸው የደረሰበትን ደረጃ የሚያሳይ እና ተጠያቂነትን ማስፈን የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመድረኩ የተሳተፉት ኤዶም ውብሸትና ፅዮን ኃይለኢየሱስ ባለስልጣኑ የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት መጀመሩ እንግልትን የሚያስቀርና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።