ቀጥታ፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ብሔራዊ የቢዝነስ ፖርታል አገልግሎቶችን አስጀመረ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችና መረጃዎችን በኦንላይን ማግኘት የሚያስችሉ ብሔራዊ የቢዝነስ ፖርታል አገልግሎቶችን አስመረቀ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ብሔራዊ የቢዝነስ ፖርታል አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል ።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በመርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ የብሔራዊ ቢዝነስ ፖርታል ዓላማ የቢዝነስ ስርዓቱን ለማሻሻል፣ ምቹና ቀልጣፋ አሰራር እንዲኖር ለማድረግ ነው።

በተለይም ተገልጋዮች የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችና መረጃዎችን በኦንላይን እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

ፖርታሉን ለመጀመሪያ ጊዜ እ.አ.አ በ2019 በማበልጸግ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ ማደረጉን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ይህም የህንጻ ግንባታ ፊቃድና ንብረት ምዝገባ አገልግሎት ላይ መዋሉን ተናግረዋል።

ብሔራዊ የቢዝነስ ፖርታል አገልግሎት ለሀገር ጠቃሚ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጫ መሆኑንም ገልጸዋል።

አገልግሎቱን የበለጠ ለማሻሻልና ወደ ሌሎች ለማስፋት ሚኒስቴሩ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመተባበር እ.አ.አ ከ2021 ጀምሮ ተጨማሪ ይዘቶችን የመጨመር ስራዎች መስራቱን ጠቅሰዋል።


 

በአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ፕሮግራም ኦፊሰር ማክዚም ሄንድሪክስ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የቢዝነስ ፖርታል አገልግሎትን ማስጀመሯ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ውጤታማ የተቋማት ስርዓት መጀመሯን ማሳያ ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፊቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የብሔራዊ ቢዝነስ ፖርታል አገልግሎትን ካስጀመሩ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ሁንዴሳ ተናግረዋል።

የብሔራዊ ቢዝነስ ፖርታል አገልግሎቱ ቀደም ሲል ረዥም ጊዜ ይፈጁ የነበሩ አገልግሎቶችን ያሻሻለ መሆኑንም ገልጸዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ብሔራዊ ቢዝነስ ፖርታል ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር የሚያስችልና ብልሹ አሰራሮችን የሚያስቀር በመሆኑ በአስተዳደሩ በመጀመሩ ደስተኛ ነን ብለዋል ።

ብሔራዊ ቢዝነስ ፖርታልን ተግባራዊ ለማድረግ ለባለሙያዎች ስልጠና የመስጠትና የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የማሟላት ስራ መሰራቱን የተናገሩት ደግሞ ከባህርዳር ከተማ አስተዳደር ህንፃ ሹም ቢሮ የተሳተፉት አቶ ደረጀ ንጉሴ ናቸው ።

አዳዲስ ይዘቶችን የጨመረው ብሔራዊ ቢዝነስ ፖርታል በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ባህር ዳር እና ድሬደዋ ከተሞች በተግባር ላይ መዋሉም ተገልጿል ፡፡

ብሔራዊ የቢዝነስ ፖርታል አገልግሎት ከቴሌብርና ሲቢኢ ብር ጋር የተሳሰረ መሆኑ ተገልጋዮች የመንግስት አገልግሎቶች በኦንላይን ማግኘትና ክፍያ መፈፀም የሚያስችላቸው እንደሆነም ተመላክቷል ፡፡

ብሔራዊ የቢዝነስ ፖርታል በቀጣይ አገልግሎቱን ወደ ሌሎች ከተሞች ለማስፋፋትም በትኩረት እንደሚሰራ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም