ቀጥታ፡

ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና የባህል ስፖርት ፌስቲቫል በመጪው ቅዳሜ መካሄድ ይጀምራል

ሆሳዕና፣ የካቲት 27/2017(ኢዜአ)--22ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና 18ኛው የባህል ስፖርት ፌስቲቫል ከየካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡

ውድድሩ "ባህላዊ ስፖርቶቻችን ለጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡ 

የውድድሩን ቅድመ ዝግጅት በማስመልከት የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽንና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይነህ ኃይሌ በመግለጫው እንዳሉት 22ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና 18ኛው የባህል ስፖርት ፌስቲቫል ከየካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በሆሳዕና ከተማ ይካሄዳል፡፡

ውድድሩ "ባህላዊ ስፖርቶቻችን ለጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን እስከ መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም ቆይታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ውድድሩ ትግል፣ ፈረስ ጉግስ፣ ገበጣና ገናን ጨምሮ በ11 አይነት የባህል ስፖርቶች የሚካሄድ ሲሆን ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ  ከ1 ሺህ 370 የሚጠጉ የስፖርት ልዑካንም እንደሚሳተፉ አስረድተዋል፡፡

በሀገሪቱ የሚገኙ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያሏቸውን ባህላዊ እሴቶች በፌስቲቫሉ ላይ በማቅረብ እንደሚያስተዋወቅ አመልክተዋል፡፡

በዚህም በተቀመጠው የመወዳደሪያ መስፈርት መሰረት ባህላቸውን በተሻለ መልኩ ያስተዋወቁ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እውቅና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ በላይነህ መርሃ ግብሩ ከስፖርታዊ ውድድር ባለፈ የእርስ በርስ ትስስርና አብሮነትን ለማጠናከርም ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።


 

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ በበኩላቸው በክልሉ ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫልና ውድድር ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት መደረጉን  ጠቁመዋል፡፡

ውድድሩ የሚካሄድባቸውን ስፍራዎች ከማዘጋጀት አንስቶ እንግዶች የሚያርፉበት ቦታ መዘጋጀቱንና እንግዶችም ከወዲሁ ወደ ክልሉ መግባት መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡

ዝግጅቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የክልሉ ህዝብ የእንግዳ ተቀባይነት ባህሉን በመጠቀም የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም