ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በማሳተፍ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ለኡጋንዳ ምሳሌ የሚሆን ነው - አምባሳደር ጆኒ ሙሂንዶ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በማሳተፍ እያከናወነች ያለችው ውጤታማ የልማት ተግባራት ለኡጋንዳ ምሳሌ እንደሚሆን በኡጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ጉዳዮች ኃላፊ አምባሳደር ጆኒ ሙሂንዶ ገለጹ፡፡     

በኡጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ጉዳዮች ኃላፊ አምባሳደር ጆን ሙሂንዶ የተመራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የዳያስፖራ አገልግሎት የልምድ ልውውጥ አድርጓል፡፡

አምባሳደር ጆኒ ሙሂንዶ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ያደረጉት የልምድ ልውውጥ ለኡጋንዳ ሰፊ ትምህርት ያገኙበት ነው።


 

በልምድ ልውውጡ ኢትዮጵያ ምቹ ፖሊሲ በመቅረጽ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገሪቷ የልማት ተግባራት ላይ በንቃት መሳተፍ እንዲችል መደረጉን ለአብነት አንስተዋል።

ይህንን ተከትሎ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በትላልቅ የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ የሚያስደንቅ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን ከልምድ ልውውጡ መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

ይህም ኡጋንዳ ተሞክሮውን በመቅሰምና ወደተግባር በመቀየር የልማት ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዛት ገልጸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ኡጋንዳ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል ።


 

የሁለቱን አገራት መልካም ግንኙነት ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውን በኡጋንዳ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ውጤታማ ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ለአብነት አንስተዋል ።

የኡጋንዳ ልዑክ ቡድን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው የሚያደርጉት የልማት እንቅስቃሴና ሌሎች ተግባራት በመደነቅ ተሞክሮውን ለመቅሰም መምጣታቸውን ተናግረዋል።

አምባሳደር ፍጹም በውጭ ሀገራት ያለው የዳያስፖራ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል በተለይም ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ፣ በሪሚታንስ ለቤተሰቦቻቸው ገንዘብ በመላክ ጨምሮ በተለያዩ በጎ ተግባራት ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ በተመለከተ ማብራሪያ  መሰጠቱን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም