በኢትዮጵያ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን የዱር እንስሳት ለመታደግ በጥናትና ምርምር የታገዘ ስራ ይከናወናል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን የዱር እንስሳት ለመታደግ በጥናትና ምርምር የታገዘ ስራ ይከናወናል
አዲስ አበባ፤የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን የዱር እንስሳት ለመታደግ በጥናትና ምርምር የታገዘ ሥራ እንደሚያከናውኑ የአንድነት ፓርኮች ኮርፖሬሽንና ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቁ።
ሁለቱ ተቋማት በዱር እንስሳት ጥበቃ፣ በትምህርትና ስልጠና ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙና የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን የተኩላ ዝርያዎች፣ የአፍሪካ ዝሆኖች፣ የጫካ ፈረስ የመሳሰሉትን የዱር እንሰሳት ለመታደግ በጋራ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል የሱፍ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው በእንስሳትና በዕጽዋት ዘርፍ ያለውን የካበተ የማስተማር ልምድ ለኮርፖሬሽኑ ለማካፈል ዝግጁ ነው።
በእንስሳት ሳይንስ ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች በዘርፉ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
በተለይም የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን የዱር እንስሳት መታደግ የሚያስችሉ ሳይንሳዊ መፍትሔዎችን በማቅረብ በጋራ እንደሚሰሩም ነው ያረጋገጡት።
የአንድነት ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ታምራት ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድረው ፓርክ በመካነ እንስሳት የተሟላ መሰረተ ልማትና ብቁ የሰው ኃይል እንዳለው ጠቅሰዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱ የፓርኩን ባለሙያዎች አቅም መገንባት የሚያስችሉ ትምህርትና ስልጠናዎችን ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ ከፓርክ አገልግሎት ባለፈ ለትምህርት ተቋማት የጥናትና ምርምር ማዕከል የሚሆን ዘመናዊ መሰረተ ልማት የተሟላላት መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ለሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።