ቀጥታ፡

በተደራጀ የግብርና መረጃ ልውውጥ ሥርዓት ዘርፉን ለማዘመን ትኩረት ተደርጓል

አዳማ፤የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦ የተደራጀ የግብርና መረጃ ልውውጥ ሥርዓትን በማስፈን ዘርፉን ለማዘመን እንደሚሰራ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት በስምንት ተቋማት መካከል የግብርና መረጃ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ሰነድ ዛሬ በአዳማ ተፈርሟል።

ሠነዱን የግብርና ሚኒስቴር፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ፈርመዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር) የግብርና ዘርፍ ተቋማት በተበታተነ መልኩ የሚያደራጁት መረጃ የጊዜና የሀብት ብክነት ከማስከተሉም በላይ አዋጭ አይደለም ብለዋል።

ስምምነቱ ይህንን አሰራር ከማስቀረት ባለፈ በዘርፉ ያሉትን መረጃዎች ወደ አንድ ቋት ተሰብስቦ ሁሉም የሚጠቀምበት ሁኔታን ለማመቻቸት ያስችላል ብለዋል።

እንዲሁም አንድ ወጥ የሆነ የግብርና ዳታን ለመለዋወጥ፣ መረጃ ላይ የተመሰረተ ስትራቴጂና ፖሊሲ ለመቅረፅ እንደሚያግዝም አስረድተዋል።

የስምምነቱ መፈረም የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን አጋዥ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬው ተገኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው የስምምነቱ ዓላማ ተቋማት የሚያገኙትንና የሚያመነጩትን ግብርናና ግብርና ነክ መረጃዎች በጋራ በመጠቀም ዘርፉን ለማዘመን መስራት ይገባል ብለዋል።

በተለይ ግብርናን ለማሻገር የሚሰሩት ስራዎች በእውቀትና በመረጃ ላይ የተመሰረቱ መሆን እንዳለባቸው ጠቅሰው በዚህ ረገድ ፍሬያማ ስራ ለመስራት ስምምነቱ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከኢንስቲትዩቱ ጋር አብረው ከሚሰሩ አካላት ጋር በመተባበርና በመነጋገር በተቋሙ የሚተገበሩ ፕሮግራም እና ፕሮጀክቶችን ስኬታማ ለማድረግ ገንቢ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ክንፈ ኃይለሚካኤል፤ ተቋሙ ለሁሉም ሴክተር ጥራት ያለው መረጃ እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው ስምምነቱም በግብርናው ዘርፍ ግብዓት የሚሆኑ መረጃ አመንጪ ተቋማት ጋር ይበልጥ በጋራ ለመስራት ያሰችላል ብለዋል።

በተለይ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ለግብርናው ዘርፍ ወሳኝ በመሆኑ በቀጣይ ስራውን ለማጠናከር የስምምነቱ ፋይዳ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

መረጃዎችን በጥራትና በወጥነት በመለዋወጥ አጠቃላይ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ስምምነቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም