ኢትዮጵያ እና ጣልያን በጉምሩክ ዘርፍ በትብብር መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መከሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ጣልያን በጉምሩክ ዘርፍ በትብብር መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መከሩ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2017 (ኢዜአ)፦ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ከጣልያን ጉምሩክ ኤጀንሲ የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር ጀኔራል አንድሪያ ማንዜላ እና በኤጀንሲው የአውሮፓ እና የዓለም አቀፍ የጉምሩክ ጉዳዮች ኃላፊ ራፋኤል ካፑአኖ (ዶ/ር) ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ውይይቱ ሁለቱ ሀገራት የጉምሩክ ተቋማት በጋራ ለመስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።
ሁለቱ ወገኖች ድንበር ዘለል፣ ዓለም አቀፍ እና በርካታ ሀገራትን የሚያስተሳስረው የጉምሩክ አገልግሎት ላይ በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑየተገለጸ ሲሆን ለዘርፉ እድገትም የሀገራት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለው የንግድ እንቅስቃሴ ፈጣን እና ተለዋዋጭ ባህሪ ያለው በመሆኑ ይህን ታሳቢ ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻልም የጉምሩክ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን እና የጣልያን ጉምሩክ ኤጀንሲም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት የሚመጥን የጉምሩክ አገልግሎት ለመስጠት በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል።
በተለይም በቴክኖሎጂ እና በአቅም ግንባታ ስራዎች የሀገራቱ የጉምሩክ ተቋማት ያላቸውን ልምድ እና ተሞክሮ ለመለዋወጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ መገለጹን ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።