የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማሳደግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ ለ49ኛ ጊዜ "ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል" በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ በመግለጫቸው፥ የቀኑ መከበር የሴቶችን ሁለንተናዊ የትግል እንቅስቃሴ ውጤት ለመዘከር፣ብሎም ሰፋፊ ንቅናቄዎችን ለማድረግና ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል።
መንግስት የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ፣በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም የአመራርና ውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን ለማሳደግ እየወሰደ ባለው ጠንካራ እርምጃ አበረታች ለውጦች መምጣታቸውን ገልጸዋል።
የሴቶችን አደረጃጀት በማጠናከር ሞዴሎችን ከመፍጠር ጎን ለጎን የቁጠባ ባህልን ለማሳደግ የተለያዩ ሰራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።
ለሴቶች የብድር አገልግሎትን በማመቻቸት በገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ መደረጉንም አብራርተዋል።
ቀኑን በማስመልክት 45 ሺህ ሴቶች በቦንድ ግዢ እንዲሳተፉ በማድረግ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቂያ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዚህም 22 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሴቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ተሳትፏቸውን በማጠናከር በሰላም ግንባታ እና ግጭት አፈታት ላይ ጉልህ ሚና ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንንም አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
ቀኑን በመላ ሀገሪቱ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፥እስከ መጋቢት 30 ቀን 2017 ደረስ በተለያዩ ዝግጅቶ እንደሚከበር ጠቁመዋል።