ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራና በሌማት ትሩፋት ፕሮግራሞቿ ውጤታማ ሆናለች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋትና መሰል ፕሮግራሞቿ ውጤታማ መሆን እንደቻለች የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በአፍሪካ ሕብረት የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ቋሚ ተወካይ አሻ መሀመድ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በምግብና ሥርዓተ-ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ላይ በትብብር መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት፣ አረንጓዴ ዐሻራና የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብሮች ውጤታማ ተግባራት ማከናወኗን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ምግብና ሥርዓተ-ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም፤ ከፈረንጆቹ 2025 እስከ 2035 በሰባት ክልሎች እንደሚተገበር ተገልጿል፡፡

ፕሮግራሙ በክልሎቹ በአየር ንብረት፣ በግጭትና በተለያየ ምክንያት የምግብ ዋስትናና የድህነት ችግር ባጋጠማቸው አካባቢዎች 15 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል፡፡

በምግብ ዋስትናና ሥርዓተ-ምግብ ላይ የሚተገበሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ይህ ፕሮግራም ተጨማሪ ዐቅም ይፈጥራል ማለታቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡

አሻ መሀመድ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ጋር አብሮ የመሥራት ጥሩ ተሞክሮ እንዳላትና አዲሱ ፕሮግራምም ውጤታማ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡

ፕሮግራሙ በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት የሚደገፍ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ በኬኒያ፣ ሶማሊያና በደቡብ ሱዳን የሚተገበር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም