ቀጥታ፡

የቃሊቲ ወደብና ተርሚናል ግንባታ በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦የቃሊቲ ወደብና ተርሚናል ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የመገንባት ስራ በይፋ ተጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የቃሊቲ ወደብና ተርሚናል ግንባታውን ከሚያከናውነው የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት የተፈራረመ ሲሆን ግንባታውንም በይፋ አስጀምሯል፡፡


 

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ(ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽመልስ እሸቱ(ኢ/ር) በቃሊቲ ወደብና ተርሚናል ስምምነቱን በመፈራረም ግንባታውን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የቃሊቲ ወደብና ተርሚናል ብዛት ያላቸው ከባድ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግድ ተርሚናል ነው ብለዋል፡፡

ሆኖም ተርሚናሉ ለወደቡ ሠራተኞች ብሎም ለአገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ምቹ ሳይሆን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይ ተርሚናሉን በዘመናዊና ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ለመገንባት ስራ መጀመሩን ጠቁመው ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለሠራተኞች፣ ለደንበኞች እና ለባለድርሻ አካላት ምቹ የሥራ አካባቢ እንዲሆን አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሽመልስ እሸቱ (ኢ/ር) በበኩላቸው ግንባታውን በተቀመጠለት ጊዜና ጥራት ለማጠናቀቅ ይሰራል ብለዋል፡፡

በግንባታው የተርሚናሉ የግቢ ውስጥ መንገድ፣ የኮንቴይነር ተርሚናል ዲዛይን እና አጠቃላይ ግንባታ የሚከናወን ሲሆን ከ510 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ጠቁመዋል፡፡

ግንባታውን በ6 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙንም በስምምነቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም