ከተሞች የኢኮኖሚ አቅማቸውን በራሳቸው ገቢ ለመሸፈን የሚያስችላቸው ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞች የኢኮኖሚ አቅማቸውን በራሳቸው ገቢ ለመሸፈን የሚያስችላቸው ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው
አሶሳ፤የካቲት 27/2017(ኢዜአ):-ከተሞች የኢኮኖሚ አቅማቸውን በራሳቸው ገቢ ለመሸፈን የሚያስችላቸው ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ አስታወቀ።
መድረኩ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በጋምቤላ ክልሎች ከሚገኙ የከተማ አስተዳዳር እና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በአሶሳ ከተማ እየመከረ ነው።
የኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም ጤናው፥ ከተሞች የውስጥ ገቢያቸውን በማሳደግ ልማታቸውን በራሳቸው አቅም መሸፈን አለባቸው።
ይህም ከተሞችን ከጥገኝነት ለማላቀቅ እና ተመጣጣኝ ዕድገት እንዲኖራቸው ያግዛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች መድረክ በከተሞች መካከል የልምድ ልውውጥ በማድረግ አቅማቸውን እንዲገነቡ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ከተሞችን ፅዱና ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በዚህ ረገድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ከተሞች በትብብር መድረኩ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ቢፍቱ ጎሹ በበኩላቸው፥ በክልሉ የሚገኙ ከተሞች አስፈላጊውን መሠረተ ልማት እንዲያሟሉ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከተሞች በመዋቅራዊ ፕላን እንዲመሩ እና የማዘጋጃ ቤቶች የፋይናንስ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግ ከተሞችን ዘመናዊ እና ምቹ ለማድረግ የክትትል ስራ እየተከናወነ እንደሆነም አንስተዋል።
ከተሞች በዕውቀት እንዲመሩ እና ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ እንዲያደርጉ የትብብር መድረኩ የሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ለከተሞች ዕድገት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውም ኢንጅነር ቢፍቱ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ የአሶሳ ከተማ ከንቲባ አብዱልከሪም አብዱረሂምን ጨምሮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የዘጠኝ ከተሞች የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ 107 ከተሞችን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን ከተሜነትን ለማስፋፋት እና የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው።