ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የመከላከያ ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በመከላከያ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር፥ ከፓኪስታን መከላከያ እና አቪዬሽን ሚኒስትር ካውጃ አሲፍ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ ሁለቱ ሀገራት መከላከያ፣ቴክኖሎጂ እና አቪዬሽን ጨምሮ በሁለትዮሽ እና በባለብዙወገን የትብብር ማዕቀፎች ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።

አምባሳደር ጀማል የኢትዮጵያ መንግስት ፓኪስታን የተባበሩት መንግስት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል መሆኗን ተከትሎ ያስተላለፈውን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ለሚኒስትሩ አድርሰዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር በአቪዬሽን፣ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎችም ያላትን ትብብር ለማጠናከር እንደምትሻ አመልክተዋል።

ሚኒስትሩ እ.አ.አ በሜይ ወር 2025 በአዲስ አበባ በሚካሄደው የኢትዮጵያን ምርቶች እና አገልግሎት የሚያስተዋውቅ ኤግዚቢሽን እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የፓኪስታን መከላከያ እና አቪዬሽን ሚኒስትር ካውጃ አሲፍ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር እንዲጠናከር እንደምትሰራ መግለጻቸውን በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም