የመድሃኒት አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመድሃኒት አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሆሳዕና፣የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ (ዶ/ር) ገለጹ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አቀፍ የጤና ኤክስቴንሽን መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡
የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር ለሚነሱ ጥያቄዎች በዘላቂነት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በሀገር ደረጃ በሁሉም መስክ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት እውን ለማድረግ ከሚደረጉ ጥረቶች አንዱ ከውጪ የሚገቡ የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተጀመረውን ሥራ ጠቅሰዋል።
በዚህም በሀገር ውስጥ መድሀኒቶችን ማምረት በመጀመሩ በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ አቅርቦት 36 በመቶ ለማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የግል ባለሀብቱ በዘርፉ እንዲሰማራ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል ሲሉም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
በማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን አባል ማድረግ እንደተቻለ የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ጋልጋሎ (ዶ/ር) ናቸው።
ከመድሃኒት ፍላጎትና አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በተለይ የሀገር ውስጥ ምርት ማጠናከሩ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፥ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ተሳትፎ መሳደግ ቀዳሚ መፍትሔ መደረጉን ተከትሎ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል።
በምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ወይዘሮ ባጠናሽ ተመስገን በበኩላቸው የጤና መድህን አገልግሎት ለብዙዎች እፎይታ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተገልጋዮች ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚያነሷቸው ቅሬታዎች መፈታት እንዳለባቸው አንስተዋል።
በሀድያ ዞን ሌሞ ወረዳ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ወይዘሮ ብዙነሽ ኪዳኔ በበኩላቸው፥ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤና የሕክምና እርዳታ በመስጠት የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ተግተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የተሟላ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የግብዓትና የመድኃኒት አቅርቦት ውስንነቶች እንዳሉ አስታውሰው፥ ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት መንግስት የጀመረውን ሥራ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።