ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል የልማት እና የቱሪዝም ልማት ስራዎችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል የልማት እና የቱሪዝም ልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአምቦ ወረዳ በነበራቸው ጉብኝት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ጋር በመሆን የኬኛ ቤቭሬጅ ፋብሪካን ተመልክተዋል።

ፋብሪካው በመጪዎቹ ሶስት ሳምንታት ውስጥ ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን ሶስት ሚሊዮን ሄክቶሊትር የማምረት አቅም እንዳለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የአስተዳደር ሥራን ወደ ሕዝብ ለማቅረብ የቀበሌዎች መጠናከር ወሳኝ ነው ያለው ጽህፈት ቤቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በየአካባቢው ለሕዝብ ቅርብ የሆነ አስተዳደር ለመፍጠር (power devolution) ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።


 

ከዚህ አንጻር በአምቦ ወረዳ የአንድ ቀበሌ እንቅስቃሴ በጉብኝት ወቅት ምልከታ ተደርጎበታል።

በቀበሌው የማብቃት ተግባር በክልሉ 7 ሺህ 342 ቀበሌዎች መደራጀታቸውንና 50 ሺህ የሰው ኃይል መመደቡ ተመላክቷል።

ከዚህ ቀደም በወረዳዎች ተማክለው የነበሩ ሙያዊና አስተዳደራዊ አገልግሎቶች በቀበሌ ደረጃ በተገቢው የሰው ኃይል እየተሰጡ እንደሚገኝ ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።


 

ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የወንጪ ደንዲ ኤኮ ሎጅ አካል የሆነው የደንዲ ክፍል ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ ተመልክተዋል።

የሥራው የሲቪል ግንባታ ሥራዎች ምዕራፍ ተጠናቆ አሁን የማጠናቀቂያ ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም