የንብረት ማስመለስ ህጉን ተፈጻሚ ማድረግ የሚያስችሉ የአሰራር ስርዓቶች እየተዘረጉ ነው - ፍትህ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የንብረት ማስመለስ ህጉን ተፈጻሚ ማድረግ የሚያስችሉ የአሰራር ስርዓቶች እየተዘረጉ ነው - ፍትህ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦የንብረት ማስመለስ ህጉን ተፈጻሚ ለማድረግ የአሰራር ስርዓቶችን እየዘረጋ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ህብረተሰቡ ''ንብረታችሁ እንዳይወረስ እናደርጋለን'' በሚል ከሚያጭበረብሩ ህገ-ወጦች እንዲጠነቀቅም ጥሪ አቅርቧል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 01 ቀን 2017 ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የንብረት ማስመለስ አዋጅን ማጽደቁ ይታወሳል።
አዋጁ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት በማፍራት በህዝብና በመንግስት ላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንዳይደርስ የሚከላከል ነው።
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ እና የህግ አርቃቂ ቡድን አባላት በንብረት ማስመለስ ህጉ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርዋል።
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ የንብረት ማስመለስ ህጉ ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን በተደራጀና ወጥ በሆነ መንገድ ለማስመለስ የወጣ ነው ብለዋል።
በተለያዩ ህጎች ውስጥ በተበታተነ መልኩ ተቀምጠው የነበሩ ድንጋጌዎች ምንጩ ያልታወቀ የመንግስትና የህዝብ ንብረት ማስመለስ ላይ ክፍተት እንዲፈጠር አድርገው እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡
ይህን ለማቃለል ራሱን የቻለ የንብረት ማስመለስ ህግ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲወጣ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
የንብረት ማስመለስ ህጉ በህገ-ወጥ መንገድ ንብረት በሚያፈሩ ሰዎች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ጠቁመው፤ "የዳያስፖራውንና የተወሰኑ ግለሰቦች ንብረትን ለመውረስ የወጣ ነው" በሚል በሚወራው የተሳሳተ ሀሳብ የተዛባ አመለካከት ሊያዝ እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ የንብረት ማስመለስ ህጉን ተፈጻሚ ማድረግ የሚያስችሉ የአሰራር ስርዓቶችን እየዘረጋ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ንብረቱ በህገ-ወጥ መንገድ እንደተገኘ የተጠረጠረ ግለሰብ ማስረጃውን ከዐቃቤ ህግ ባለፈ ለፍርድ ቤት ጭምር ማቅረብ እንደሚችል ጠቁመው ፤በፍርድ ቤት ውሳኔ ያልተሰጠበት ንብረት እንደማይወረስም ነው ያብራሩት።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፣ የህጉን መጽደቅ ተከትሎ አንዳንድ አካላት ንብረታችሁ እንዳይወረስ እናደርጋለን በሚል ሕብረተሰቡን ለማጭበርበር የሚሰሩ ግለሰቦች መኖራቸው እንደተደረሰበትም ነው ያነሱት፡፡
ንብረት የማጣራትም ሆነ የመውረስ ስልጣን በህግ የተሰጠው የፍትህ ሚኒስቴር መሆኑን ገልጸው፤ ህብረተሰቡም ይህን በመገንዘብ የማጭበርበር ድርጊት ከሚፈጽሙ አካላት ራሳቸውን እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የንብረት ማስመለስ ህጉ አርቃቂ ቡድን አባላት መካከል ሃወኒ ታደሰና የአለምታሪክ ሽመልስ በበኩላቸው በወንጀል የተገኘን ንብረት ለማስመለስ ወጥ የሆነ የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ አፈጻጸም ላይ ክፍተቶች ይስተዋሉ እንደነበር ገልጸዋል።
በምክር ቤቱ ያወጣው የንብረት ማስመለስ ህግ እነዚህን ክፍተቶች የሚሞላና ኢ-ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በሚገድብ መልኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።