ቀጥታ፡

የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ እንደሚፈልጉ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

33ኛው እስያ፣ አረብ እና አፍሪካ የኢንቨስትመንት ፎረም በቶኪዮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተካሄዷል።

በፎረሙ ላይ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የጃፓን ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።

ባለሀብቶቹ በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ላይ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው እና ለቅድመ-ኢንቨስትመንት ጥናት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ገልጸዋል።


 

በማምረቻ ፤ በንግድ ፤ ሎጂስቲክስ እና በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ጥናት እንደሚያደርጉም አመልክተዋል።

ባለሃብቶቹ በውይይቱ በኢትዮጵያ ስራቸውን ለማከናወን የሚያስችል የሰለጠነ ወጣት የሰው ኃይል፤ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ፤ ሰፊ የሀገር ውስጥና የውጪ ገበያ መዳረሻ ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተገነቡ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ነጻ ንግድ ቀጣና እንዳለ መረዳታቸውን ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኮርፓሬሽኑ የባለሀብቶቹን የኢንቨስትመንት ሂደት ቀልጣፋ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ኮርፓሬሽኑ ባለፉት ጥቂት አመታት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና ድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጣና የጃፓን ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።

በኢትዮጵያ ከ450 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ያስመዘገቡ 22 በጃፓናውያን እና በኢትዮጵያውያን ሽርክና ተቋቁመው ስራ መጀመራቸውንም ነው ያስታወቀው።

ኮርፖሬሽኑ ከሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ በቦሌ ለሚ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን የሚስጥራዊ ህትመት ለማከናወን ከመንግስት ተቋማት ጋር በሽርክና እየሰራ ያለው ቶፓን ግራቪቲ እና በሃዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የሶላር ፓኔል ለማምረት የሙከራ የምርት ሂደት የሚገኙው ቶዮ ሶላር ለአብነት ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም