የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሩፑን ኢንዱስትሪዎች ወደ ትርፋማነት አሸጋግሯል - አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2017(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ምርታማነትና ትርፋማነት ማሸጋገሩን የግሩፑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ ገለጹ፡፡

የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ላይ ከስያሜ ጀምሮ ተቋማዊ ማሻሻያ በማድረግ ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ ያስቻለ አዲስ አደረጃጀት ተፈጥሯል።

ባለፉት ዓመታት የመከላከያ፣ የኮንስትራክሽን፣ የግብርና እና ሌሎች ማሽነሪዎችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን በዘጠኝ ዘርፎች በማደራጀት የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ እንዲወለድ ያስቻለ ስኬታማ ለውጥ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

ግሩፑ በተኪ ምርት ተገቢውን የገበያ ድርሻ መያዝ፣ ስራ ዕድል መፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ አብዮት የማቀላጠፍ ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ኪሳራ ይደርስባቸው የነበሩትን ኢንዱስትሪዎቹን ወደ ሥራ በማስገባት ትርፍ ማስመዝገብ መጀመሩንም ነው የጠቀሱት፡፡

የውጭ ምንዛሬ እና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ፈታኝ እንደነበር የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉ እና የኢንቨስትመንት ሆልዲንግን መቀላቀላቸው ችግሩን በመፍታት ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገሩ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

ከፋይናንስ ተቋማት በቂ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት በመገኘቱ የአዳማ የግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ወደ ተሟላ የምርት ሂደት መግባቱን ገልጸዋል፡፡

ኢንዱስትሪው ትራክተር፣ የሰብል መሰብሰቢያ ማሽንና እና የመስኖ ፓምፖችን በማምረት ለዘመናዊ ግብርና እና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ገንቢ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ እና የደብረ ብርሃን የኮንስትራክሽን ማምረቻ ኢንዱስትሪዎችም ወደተሟላ ምርት መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

አምባሳደር ሱሌማን አክለውም በተቋሙ ስትራቴጂክ ዕቅድ መሰረት ከሊቲዬም ማዕድን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ ማምረት የሚያስችል ፋብሪካ ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በሊቲዬም ማዕድን ላይ ዕውቀትና ክህሎት ካላቸው የውጭ ኩባንያዎች ጋር በጥምረት በመስራት የብረታ ብረት ኩባንያዎችን ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ በሀገር ውስጥ በሚገጣጠሙ ተሽከርካሪዎች እና ማሽነሪዎች ላይ የዕውቀት ሽግግር ለመፍጠር ከቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት እየተፈራረመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም