ቀጥታ፡

የስደተኞችና የተቀባይ ማህበረሰብ በልማት መተሳሰር ዲፕሎማሲንና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን አጎልብቷል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የተጠለሉ ስደተኞች ከተቀባይ ማህበረሰብ ጋር ያላቸው የጋራ ልማት እንቅስቃሴ በዲፕሎማሲና በህዝብ ለህዝብ ትስስር ስኬታማ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን ገለጹ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን፤ ኢትዮጵያ ስደተኞችንና ተመላሾችን በማስተናገድ በኩል ከለውጡ በኋላ ያስመዘገበችውን ስኬት በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ በማብራሪያቸው እንደገለጹት፤ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ በሚፈጠር ችግር፣ ድርቅና ተያያዥ ሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ለሚሰደዱ የውጭ ሀገር ዜጎች ከለላ በመስጠት በዓለም አቀፍ ደረጃ በበጎ ተግባር የምትታወቅ ሀገር ናት።

የጎረቤት እና የመካከለኛው ምስራቅን ጨምሮ ከ34 አገሮች በላይ የመጡ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ባለይ ዓለም አቀፍ ስደተኞችን በመቀበል ተገቢውን መስተንግዶ እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።

የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋን በመሸሽ ለመጡ ስደተኞችም ህጋዊ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቷን ጠቁመው፤ ከአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ስደተኛን ማስተናገድ ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በመንግስታቱ ድርጅትና በአፍሪካ ሕብረት ሕግጋት ስምምነቶች መነሻነት እየተስተናገዱ መሆኑን አንስተዋል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በስደት ላይ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን እንዲመለሱ ያደረጉት ጥረትም ለዜጎቿ የተሰጠውን ክብር እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

በዚህም በለውጡ ማግስት ኢትዮጵያ ለዜጎቿና ዓለም አቀፍ ስደተኞች የሰጠችው ሰብዓዊ ክብር የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ውጤት ተደርጎ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ ዓለም አቀፍ ስምና ዝናዋን አስጠብቃ እየቀጠለች እንደምትገኝም ዋና ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ዓለም አቀፍ ስደተኞች ከተቀባዩ ማህበረሰብ ጋር በልማት ስራ ጭምር ተሰናስለው እንዲኖሩ በመደረጉ የዲፕሎማሲና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ያጠናከረ ስኬት ማስመዝገቡ መቻሉን ተናግረዋል።

ለሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ሌሎች አገራት ስደተኞች የሚደረገው ማህበራዊና መሰረታዊ የሰብዓዊ ድጋፍም ወደ አገራቸው ሲመለሱ የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲሆኑ ያስቻለ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

ለስደተኞች የሚሰጠው ተገቢ ከለላና ቅበላም የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲዊ ትብብር የማጠናከር መርህ በማስቀጠል ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሚኖሩ ዓለም አቀፍ ስደተኞችንም ከተቀባዩ ማህበረሰብ ጋር በልማት ስራዎች ተሰናስለው በመሰማራት ተጠቃሚ የሆኑበት ስኬታማ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም