የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ቴክኖሎጂና የመረጃ ስርዓት ትግበራ አርዓያነት የሚወሰድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ቴክኖሎጂና የመረጃ ስርዓት ትግበራ አርዓያነት የሚወሰድ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ግብርናን ለማዘመን የተገበረችው የቴክኖሎጂና የመረጃ ስርዓት ተሞክሮ የሚወሰድበት ተግባር መሆኑን በዓለም ባንክ የገጠር ልማት እና አስተዳደር መሪ ፓርሜሽ ሻህ ገለጹ።
የመጀመሪያው የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የስርዓተ ምግብ ከፍተኛ የመማማሪያ መድረክ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።
መድረኩን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ)፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የግብርና ምርምር እና ልማት ማስተባበሪያ እና የዓለም ባንክ በጋራ አዘጋጅተውታል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ የልማት አጋሮች እና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው።
በዓለም ባንክ የገጠር ልማት እና አስተዳደር መሪ ፓርሜሽ ሻህ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በግብርና ዲጂታላይዜሽን ላይ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች የምክር አገልግሎት እየሰጠች ነው።
በዚህም የአፈር መረጃ እንዲሁም የአፈር ካርታ ዲጂታላይዝ ማድረግ መቻሏን አንስተዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ ዝርያዎችን ከአርሶ አደሮች ጋር በማስተዋወቅ አርሶ አደሮቹ እንዲያላምዷቸው መደረጉን ገልጸዋል።
በርካታ አርሶ አደሮች በአየር ንብረት መረጃ ላይ ተመስርተው ባገኙት ምክር መሰረት የመፍትሄ ሃሳቦችን በመተግበር ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፤ እነዚህ ተግባራት ትምህርት የሚወሰድባቸው መሆኑን አንስተዋል።
የተለያዩ የአፍሪካ አገራት በግብርና ዲጂታላይዜሽን ላይ እየሰሩ እንደሚገኙና በዚህም የመረጃ ጥራትን በማስፋት ለአርሶ አደሮች የተሻለ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም በግብርናው ላይ ሰፋፊ ኢንቨስትመንት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ እድገትም እየተመዘገበባቸው መሆኑን አመላክተዋል።
በዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣናዊ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ አስተባባሪ ዳዊት ሠለሞን (ዶ/ር) ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ ትልቅ ፈተና መኖሩን አንስተዋል።
ይህ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለማቃለል እና ችግሩን ለመቋቋም በቴክኖሎጂ እና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ስርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መጀመሪያው የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የስርዓተ ምግብ ከፍተኛ የመማማሪያ መድረክ በነገው እለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።