የካራማራ ድል የመላው ኢትዮጵያውያን የትብብር ውጤት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የካራማራ ድል የመላው ኢትዮጵያውያን የትብብር ውጤት ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2017(ኢዜአ)፦የካራማራ ድል የመላው ኢትዮጵያውያን የትብብር ውጤት ነው ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ገለጹ።
47ኛው የካራማራ ድል የመታሰቢያ በዓል በአዲስ አበባ የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት አደባባይ በድምቀት ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የቀድሞ ሰራዊት አመራሮችና አባላት፣ የመንግስት ተወካዮችና የኩባ ሪፐብሪክ አባላት፣ አምባሳደሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የካራማራ ድል የጀግኖች ኢትዮጵያዊያን የመስዋዕትነት ውጤት ነው።
የአሁኑ ትውልድ የአባቶችን የድል መንፈስ በመውረስ ለሁለንተናዊ ድል መተባበር እና መረባረብ እንደሚጠበቅበትም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር መይሊን ሱዋሬዝ አልቫሬዝ በበኩላቸው የኩባ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ታሪካዊ መሆኑን ገልጸዋል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሀገራቸው እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።