ህብረተሰቡ ለአካባቢ ጥበቃ ስራ የድርሻውን እንዲወጣ ለማድረግ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ ለአካባቢ ጥበቃ ስራ የድርሻውን እንዲወጣ ለማድረግ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2017(ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ለአካባቢ ጥበቃ ስራ የድርሻውን እንዲወጣ ለማድረግ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ወሳኝ ነው ሲሉ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤና የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሌሊሴ ነሜ ፈርመውታል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ያለ ህብረተሰቡ ተሳትፎ ማሳካት አዳጋች ነው።
በዚህ ረገድ ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ለአካባቢ ጥበቃ ስራ የድርሻውን እንዲወጣ የመገናኛ ብዙሃን ትልቅ ሚና እንዳላቸውም አመልክተዋል።
በመላ አገሪቷ ተደራሽና አስተማማኝ የዜና ምንጭ ከሆነው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በጋራ መስራት ባለስልጣኑ የያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚያስችለውም ነው ዋና ዳይሬክተሯ ያብራሩት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአካባቢ ጥበቃና በጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የተጀመሩ ኢኒሼቲቮችን ለማስቀጠል በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ማከናወን አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄዎችን በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ ከኢዜአ ጋር በጋራ መስራት ውጤታማ ያደርገናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው ኢዜአ በተለያዩ አማራጮች የአካባቢ ጥበቃን ስራ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በትጋት ይሰራል ብለዋል።
በቅርቡ በተለያዩ ቋንቋዎች በጀመራቸው የይዘት አማረጮች ለሌሎች አገራት መገናኛ ብዙሃን ተደራሽ በማድረግ የባለስልጣኑን ተልዕኮ እንዲሳካ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።