የልማት ፕሮጀክቶችን በሁሉም አካባቢዎች በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የልማት ፕሮጀክቶችን በሁሉም አካባቢዎች በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት መስራት ይገባል
አዲስ አበባ፤የካቲት 26/2017(ኢዜአ):-የልማት ፕሮጀክቶችን በሁሉም አካባቢዎች በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) ገለጹ።
በክልሉ በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር፥ የልማት ፕሮጀክቶችን በሁሉም አካባቢዎች በፍትሃዊነት ተደራሽ ማድረግ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
እያደገ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት ለማሟላት በፕሮጀክት አስተዳደር ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን አስቀድሞ መፍታት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የልማት ፕሮጀክቶችን የግንባታ ሂደት ከሚያጓትቱ ጉዳዮች ውስጥ የወሰን ማስከበር እና የካሳ ክፍያ ተጠቃሽ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ አመራሩ ጉዳዮቹ እልባት እንዲያገኙ በልዩ ትኩረት መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
የተጀመሩ መንገዶች በፍጥነት ከማጠናቀቅ አንጻር ያለውን ውስንነት እንዲፈታም አሳስበዋል።
በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን እንዲፈቱ እና ከኮሪደር ልማት ስራ ጋር በተያያዘ በተመረጡ አራት ከተሞች እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ መስራት እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር መሀመድ አብዱራህማን (ኢ/ር) እንደገለጹት የተጀመሩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በልዩ በትኩረት መስራት ይገባል።
የመንገድ መሰረተ ልማት ፍላጎት ላመሟላት የሁሉንም አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።
በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት በየፕሮጀክት የመፈጸም እና የማስፈጸም አቅምን ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል።
በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ የካሳ እና የወሰን ማስከበር ችግሮችን በመፍታት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
የህብረተሰቡን የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ መመለስ አብይ ጉዳይ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ የፕሮጀክት አስተዳደር አቅምን በማሳደግ ለውጤታማነቱ መስራት ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የፌደራል ፣ የክልል እንዲሁም ከዞኖች እና ከልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።