ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥምን የእናቶች ሞት ለመከላከል የባለድርሻ አካላት አስተዋጾኦ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥምን የእናቶች ሞት ለመከላከል የባለድርሻ አካላት አስተዋጾኦ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
አዲስ አበባ፤የካቲት 26/2017(ኢዜአ)፦ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥምን የእናቶች ሞት ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጾኦ ማድረግ እንዳለባቸው የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
ከወሊድ በኋላ ለሚያጋጥሙ ከፍተኛ ደም መፍሰስ ሁሉን አቀፍ ጥቅል ሕክምና በተወሰኑ ጤና ተቋማት ትግበራ በይፋ ተጀምሯል።
የጤና ሚኒሰትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በወቅት እንደገለጹት፥ መንግስት የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የእናቶች ሞት ምጣኔን በከፍተኛ መጠን መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ፥ አሁንም ግን ልንከላከላቸው በሚችሉ ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር ተያይዞ በሚመጡ የጤና እክሎች እናቶች አልፎ አልፎ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ተናግረዋል።
በተለይ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ከፍተኛ ደም መፍሰስ ለእናቶች ሞት ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ አገራዊ እቅድ ተዘጋጅቶ ለሕክምና የሚያስፈልጉ ግብአቶች በበቂ ሁኔታ በአገራችን እንዲኖር የሚያስችል ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዛሬም የእናቶች ሞትን ለመቀነስ ከወሊድ በኋላ ለሚከሰት ደም መፍሰስ ሁሉን አቀፍ ጥቅል ሕክምና ትግበራ ይፋ መደረጉን አንስተዋል።
ይህ ትግበራ ውጤታማ ሆኖ የእናቶችን ሞት በተፈለገው ደረጃ ለመቀነስና ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጾኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ሄልዝ ኬር ሲስተም ኢምፓክት ሴንድኬት አፍሪካ (ACSIS) ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር እሰማሄል ሸምሰዲን በበኩላቸው፥ ትግበራው ድህረ ወሊድ የሚመጣ የእናቶችን ሞት በተፈለገው ደረጃ ለመቅረፍ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ይህ ተግባራዊ ሆኖ ውጤታማ እንዲሆን በጋራ ለመስራት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፥ ለውጤታማነቱ በጋራ ለመስራት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።
በማስጀመሪያ ስነስርዓቱ የተገኙት ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በይፋ የተጀመረው ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ሁሉን አቀፍ ጥቅል ሕክምና ትግበራው በቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ እና በአምስት ጤና ጣቢያዎች በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ ውጤት እንደተመዘገበበት በወቅቱ ተመላክቷል።
በጤና ሚኒስቴር እና በሔልዝኬር ኢምፓክት ሴንዴክት አፍሪካ በተዘጋጀው የማስጀመሪያ ፕሮግራም የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።