ጥራት መንደር ዘመኑ የደረሰበትን የጥራት ደረጃ ያሟላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሀብት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጥራት መንደር ዘመኑ የደረሰበትን የጥራት ደረጃ ያሟላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሀብት ነው
አዲስ አበባ፤የካቲት 26/2017(ኢዜአ)፡- የጥራት መንደር ዘመኑ የደረሰበትን የጥራት ደረጃ ያሟላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሀብት መሆኑን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ ገለጹ።
የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ (ዶ/ር) ከፓን-አፍሪካ የጥራት መሰረተ ልማት የጋራ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ ለጋራ ኮሚቴው የጥራት መንደርን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የጥራት መንደሩ በስምንት ቢሊዮን ብር ወጪ መገንባቱን ገልጸዋል።
የጥራት መንደሩ የደረጃዎች ኢንስቲትዩትን ጨምሮ አምስት ተቋማትን በውስጡ መያዙን አመልክተዋል።
መንደሩ የኢትዮጵያ ትልቅ ብሄራዊ ሀብት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ ስለ ኢንስቲትዩቱ በሰጡት ማብራሪያ ተቋሙ ከ50 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ልምድ ያለው እና በሰባት ቁልፍ ዘርፎች ብሔራዊ ደረጃዎችን በማውጣት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የደረጃዎች ተቋም እና የአፍሪካ የደረጃዎች ድርጅት አባል በመሆን የደረጃዎች አቅሟን ለማጠናከር እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ጥናት እና ምርምር በማድረግ የደረጃዎች ተፈጻሚነት እንዲሻሻል ድጋፍ እንደሚያደርግ እና የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝም ነው ያብራሩት።
የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የጥራት መንደሩ እና ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች እንደሚጠቀሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ከኢኒስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።