ቀጥታ፡

በአፋር ክልል ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ በሚያደርጉ የንቅናቄ ተግባራት ይከበራል

ሰመራ ፤ የካቲት 26/2017(ኢዜአ)፡-  በአፋር ክልል የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ በሚያደርጉ የንቅናቄ ተግባራት እንደሚከበር የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው "ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል" በሚል መሪ ሐሳብ  የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ  በመግለጫቸው እንዳሉት የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የክልሉን ሴቶች በሚያሳትፉና ተጠቃሚ በሚያደርጉ ልዩ ልዩ ሁነቶች ይከበራል።

ከተግባራቱ መካከል የሴቶች የልማት ቡድኖችን በመለየት በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው አደረጃጀቶችን ዳግም በማጠናከር እንደሚከበር ጠቅሰዋል።

"በንቅናቄው የሴቶች የቁጠባ ባሕል እንዲዳብር ይደረጋል" ያሉት ሃላፊዋ፤ በዚህ መርሃ ግብር ሴቶቹ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እንዲቆጥቡ የሚሰራ ሲሆን ለ210 ሴቶችም በዚሁ የንቅናቄ መርሃ ግብር የስራ ዕድል እንደሚፈጠር ገልጸዋል።

ወደ ሥራ ለሚገቡ ሴቶች ደግሞ ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በመነጋገር የብድር አገልግሎት እንደሚመቻች በማውሳት።

በዚሁ የንቅናቄ መርሃ ግብር  እስከ  200 ሺህ ለሚሆኑ የክልሉ ሴቶች የማህፀን በር ጫፍ ካንሰርና የጡት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠትና ሁለት ሺህ ለሚሆኑት ደግሞ በተመረጡ ማዕከላት የጤና ምርመራ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።

ሌላው በሳምንቱ ከሚከናወኑት ተግባራት ሴቶች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ማጠናከር ሲሆን በዚህ የንቅናቄ መርሃ ግብር 500 የክልሉ ሴቶች የቦንድ ግዥ እንደሚፈፅሙ አስታውቀዋል።

በዘንድሮው የሴቶች ቀን አከባበር ከመድረክ ባሻገር የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የሚያሳዩና የሚያሳድጉ ዐውደ ርዕዮችና ባዛሮች የሚከፈቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሞዴል ቀበሌዎች ደግሞ የሚጎበኙ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም