መገናኛ ብዙሀን ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሀን ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው
አዲስ አበባ፤የካቲት 26/2017(ኢዜአ)፡-መገናኛ ብዙሀን በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አዎንታዊ ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የሰላም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።
የሰላም ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን መገናኛ ብዙሀን በሰላም ግንባታ ዙሪያ የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ አስመልክቶ ከንግድ መገናኛ ብዙሀን ጋር ምክክር እያካሔዱ ነው።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፥ መንግስት የዜጎችን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እና አገራዊ አንድነትን ለማስቀጠል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
ከዚህ ውስጥም ባህላዊ የሰላምና እርቅ እሴቶችን ጥቅም ላይ ማዋል፤ የውይይት መድረኮችን የማመቻቸት፣በሰላም ዙሪያ ጥናቶችን ተግባራዊ ማድረግ እና የአገራትን መልካም ተሞክሮ መቀመር ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ይህም እንደ አገር እየተከናወነ ላለው የሰላም ግንባታ ስራ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ነው የጠቀሱት።
መንግስት የዜጎችን ሰላምና የአገርን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸው ተግባራት በታለመው ልክ ስኬታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።
ለዚህም መገናኛ ብዙሀን ያላቸውን ተደራሽነት በመጠቀም በሰላም ግንባታ ስራው ላይ የሚያከናውኑትን ተግባር ማጠናከር እንዳለባቸው ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።
ሚኒስቴሩ በዚህ ረገድ ከሀይማኖት ተቋማት፣ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ከመገናኛ ብዙሀንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
የምክክር መድረኩ የንግድ መገናኛ ብዙሀን በሰላም ግንባታ ዙሪያ መግባባትና በቅንጅት የመስራት ልምድ ማዳበር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በመሆኑም ለአገር አዎንታዊ ሰላም መረጋገጥ መገናኛ ብዙሀን የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት ለመወጣት በኃላፊነት እንዲሰሩ ነው ያሳሰቡት።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ሙያዊ ስነ-ምግባርን ያከበረ፣ ወቅታዊ፣ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙሃን እንዲኖሩ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ሀሰተኛ መረጃን እና የጥላቻ ንግግርን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙሀንን ተጠያቂ የማድረግና የመቆጣጠር ስራውም በትኩረት እየተሔደበት መሆኑንም እንዲሁ።
ባለስልጣኑ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ ቅንጅታዊ አሰራሮችና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማመቻቸት ለሰላም ግንባታ ስራው የሚጠበቅበትን ሀላፊነት እየተወጣ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በምክክሩ ላይ የንግድ መገናኛ ብዙሀን ተወካዮች፣የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።