ቀጥታ፡

ከለውጡ ወዲህ የተገነቡት ዘመናዊ ራዳሮች ፈጣንና ተዓማኒ የአየር ትንበያ መረጃ እየሰጡ ነው

አዲስ አበባ፤የካቲት 26/2017(ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ የተገነቡ አራት ዘመናዊ ራዳሮች በ 250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ፈጣንና ተዓማኒ የአየር ትንበያ መረጃ እየሰጡ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የትንበያ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፥ተዓማኒና ፈጣን የአየር ትንበያ መረጃ ለመሰብሰብ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ወቅቱን የጠበቀ ፈጣንና ተዓማኒ የሜቲዎሮሎጂ መረጃ ለማቅረብ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ እያዋለች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በተለይ ከለውጡ ወዲህ የተሟላ የአየር ትንበያ መረጃ መስጠት የሚያስችሉ ዘመኑን የዋጁ የትንበያ ቴክኖሎጂዎች ተገንብተው ጥቅም ላይ መዋል ጀምረዋል ብለዋል፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት ዘመኑ የደረሰበትን ደረጃ የሚያሳዩ 310 የአየር ትንበያ መሳሪያዎች ተተክለው ጥቅም ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

የአየር ትንበያ መመዝገቢያ ቴክኖሎጂዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ እና ድርቅን አስቀድሞ መተንበይና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎችን ለመስራት የጎላ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ የተገነቡ አራት ዘመናዊ ራዳሮች በ 250 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ የአየር ጠባዩን በመመዝገብ ፈጣንና ተዓማኒ የአየር ትንበያ መረጃ እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም አገልግሎቱን የበለጠ ለማዘመን ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ፣ መቀሌ እና በነገሌ ለአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ትንበያ የሚያግዙ የከፍታ የአየር መመዝገቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም