ኢትዮጵያ እና ኢኮዋስ የጋራ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ኢኮዋስ የጋራ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እና የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) የጋራ ጥቅምን ባከበረ መልኩ የሁለትዮሽ እና የባለብዝሃ ወገን ትብብራቸውን ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በናይጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ለገሰ ገረመው ከምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ኮሚሽን የቀጣናዊ ትብብር ፕሬዝዳንት ኦማር አሊዩ ቱራይ (ዶ/ር) ጋር በተቋሙ ዋና መቀመጫ አቡጃ ዛሬ ተወያይተዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ኢኮዋስ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እንዲሁም ቀጣናዊ ሰላም እና ደህንነትን ጨምሮ አጠቃላይ ትብብራቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
አምባሳደር ለገሰ እና ፕሬዝዳንት ኦማር በኢትዮጵያ እና በምዕራብ አፍሪካ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።
ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው ቀጣናዊ እና ከዛ የተሻገሩ የጋራ ፈተናዎችን ለመፍታት የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል።
ፕሬዝዳንት ኦማር ለአምባሳደሩ፥ ኮሚሽኑ በምዕራብ አፍሪካ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር እና በኢኮዋስ ቀጣና ነጻ የሰው እንቅስቃሴን የተሳለጠ እንዲሆን በማድረግ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በውይይቱ ወቅት ሁለቱ ወገኖች ትብብራቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው አማራጮች ዙሪያ መክረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ እና ኢኮዋስ በቀጣናዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች፣ ተለዋዋጭ በሆነ የዓለም የጂኦፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን በሚያረጋግጡ ዓለም አቀፍ የትብብር ማዕቀፎች ላይ ተቀራርቦ ለመስራት ተስማምተዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ እና የኢኮዋስ ኮሚሽን ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር እና በአፍሪካ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ በአቡጃ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።