ተተኪ የቅርጫት ኳስ ስፖርተኞችን ለማፍራት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው-ፌዴሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
ተተኪ የቅርጫት ኳስ ስፖርተኞችን ለማፍራት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው-ፌዴሬሽኑ
ወልቂጤ ፤የካቲት 25/2017 (ኢዜአ):-ተተኪ የቅርጫት ኳስ ስፖርተኞችን ለማፍራት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ ።
3ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
ውድድሩ እየተካሄደ የሚገኘው "ስፖርት ለሰላም፣ ለልማት፣ ለአንድነትና ለገፅታ ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
በወቅቱም የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን የውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳዊት አሳምነው እንዳሉት እንደሀገር በዘርፉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ከእነዚህም አንዱ ስፖርተኞች ራሳቸውን የሚፈትሹበትና የሚበቁበት ውድድር ማዘጋጀት መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም አሁን እየተካሄደ የሚገኘውን የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ውድድሩን ወደ ክልል ከተሞች በመውሰድ መነቃቃትን መፍጠርና ባለሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩና ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የውድድሩ 1ኛና 2ኛ ዙር ጨዋታዎች በአዲስ አበባ የተካሄዱ ሲሆን 3ኛው ዙር ደግሞ በወልቂጤ ከተማ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስራት ታደለ በበኩላቸው ውድድሩ አብሮነትና የእርስ በርስ መቀራረብ እንዲኖር ፋይዳው የላቀ መሆኑን አመልክተው ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትም ጥሩ እድልን እየፈጠረ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የቅርጫት ኳስ ስፖርት በከተማው ህዝባዊ መሰረት በማስያዝ ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ቡድን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
ከውድድሩ ተሳታፊዎች መካከል ኢንስትራክተር ዘመዴ በቀለ እንዳሉት የወልቂጤ ከተማ ህዝብ ስፖርት ወዳድ በመሆኑ በከተማው ውድድሩ መዘጋጀቱ ደስተኛ እንዳረጋቸው ገልጸዋል።
ህዝባዊ መሰረት በማስያዝ ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ቡድን ለመፍጠር የሚሰራው ስራ የሚበረታታ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ የሀዋሳ ከነማ ተጨዋች ሊድያ ቱሉ በተለያዩ ከተሞች በዚህ መልኩ ውድድሩ መዘጋጀቱ ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁማለች።
በውድድሩም አዲስ አበባን ጨምሮ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማና አማራ ክልሎች ስድስት የወንድ እና አምስት የሴት ክለቦችን እያሳተፉ ነው።
የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ/ም የጀመረው ውድድሩ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ/ም ፍጻሜውን ያገኛል።