ቀጥታ፡

በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በመደራጀት በዶሮ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ወጣቶች ተናገሩ

አዲስ አበባ፤የካቲት 25/2017(ኢዜአ)፦በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ለዶሮ ልማት የተሰጠው ትኩረት ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን በዶሮ እርባታ የተሰማሩ ወጣቶች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2015 ዓ.ም የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ማስጀመራቸው ይታወሳል።

የመርሃ-ግብሩ ዋነኛ ግብ፤ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ እና ስርዓተ ምግብን ማሻሻል ነው።

በዚህም መሰረት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዜጎች በስጋ፣ እንቁላል፣ ማር እና በወተት አምራችነት በስፋት በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ሎማ ቦሳ ወረዳ ቱለማ ጣማ ቀበሌና የአካባቢው የባለሙያዎች የአንድ ቀን ጫጩት አሳዳጊ ኃላፊነቱ የተወሰነ መለስተኛ የሕብረት ሥራ ማኅበር አባላት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በዚህም የማኅበሩ ሰብሳቢ ወጣት ማንደፍሮ አየለ፥ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ለዶሮ ልማት የተሰጠው ትኩረት የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጿል።

ሌላኛው የማኅበሩ የቁጥጥር ኮሚቴ ኃላፊ ኤሊያስ ዑቴ፥ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቅን 15 ወጣቶች ተደራጅተን ወደስራ በመግባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማስመዝገብ ችለናል ብሏል።

በአንድ ቀን ጫጩት ማሳደግ ማኅበር ተደራጅተን ወደስራ ከመግባታችን በፊት በምጣኔ ሃብት ትምህርት ተመርቄ ስራ አጥ ነበርኩ ያለው ደግሞ ሌላኛው የማኅበሩ አባል አድማሱ ግዛው ነው።

የማኅበሩ አባላትም መንግስት ባደረገላቸው ተከታታይ ክትትልና ድጋፍ በሶስት ዙር የአንድ ቀን ጫጩቶችን በማሳደግ የካፒታል አቅማቸውን ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር በማሳደግ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጿል።

በቀጣይም የማኅበራቸውን የገቢ አቅም በማሳደግ ትርፋማነታቸውን የበለጠ ለማሳደግ እየተጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የዳውሮ ዞን ግብርና መምሪያ በበኩሉ በሌማት ትሩፋት የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች በገበያ አቅርቦት ፍላጎት ላይ አዎንታዊ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን አስታውቋል።

የዳውሮ ዞን ግብርናና አካባቢ ጥበቃ መምሪያ የእንስሳት ዓሳ ሃብት ዘርፍ ኃላፊ አስፋው ጩራሞ በበኩላቸው ባለፉት ሶስት ዓመታት የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በዶሮ፣ በወተት፣ በዓሳ፣ በእንስሳት ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነት ላይ ስኬት ተመዝግቧል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ በከተማና ገጠር ኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ከአንድ ሺህ በላይ የስራ ዕድል ተጠቃሚ ወጣቶች የገበያ አቅርቦትና ፍላጎትን ምላሽ በመስጠት አዎንታዊ ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

አርሶ አደሮችም በአካባቢያቸው ጸጋዎች ልክ በመንደር ክላስተር ተደራጅተው በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተጠቃሚ እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተነሳሽነትም የዜጎችን የምግብና የሥነ-ምግብ ሥርዓት በማሻሻል መልካም አጋጣሚ እየፈጠረ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም