መንግሥት የዲሞክራሲ ተቋማት በራሳቸው አዋጅ የሚተዳደሩበትንና በገለልተኛነት የሚሰሩበትን እድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት የዲሞክራሲ ተቋማት በራሳቸው አዋጅ የሚተዳደሩበትንና በገለልተኛነት የሚሰሩበትን እድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2017(ኢዜአ)፡-በለውጡ መንግሥት የዲሞክራሲ ተቋማት በራሳቸው አዋጅ የሚተዳደሩበትንና በገለልተኛነት የሚሰሩበት እድል መፈጠሩን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በኢፌዲሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 15 መሰረት በአዋጅ ቁጥር 211/1992 የተቋቋመ ህገ መንግስታዊ የዲሞክራሲ ተቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ቁጥር 1142//2011 መሰረት አስተዳደራዊ በደልን አስቀድሞ መከላከል እና ተፈጽሞ ሲገኝ በፍጥነት እንዲታረም ለማድረግ የተቋቋመ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን አስተዳደራዊ በድሎችን በመመርመር የመፍትሔ ሀሳብ የማቅረብ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
በአስፈፃሚ ተቋማት ላይ የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን የመመርመር፣ ጥናት የማድረግ፣ ግንዛቤ የመፍጠር እና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ቁጥር ሶስትን የመቆጣጠር ሚና ያለው ነፃና ገለልተኛ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ህገ መንግስታዊ እና ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ እንዲሁም የኃላፊዎች አሿሿም በውድድር መሆኑን አንስተዋል።
ሰራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደማይችሉ ጠቅሰው፤ በአስፈፃሚ አካላት ዘንድ የሚደርሱ ቅሬታዎችን ያለማንም ጣልቃ ገብነት መርምሮ ውሳኔ እንደሚሰጥም ጠቅሰዋል፡፡
የለውጡ መንግሥት እንደ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ላሉ ሌሎች የዲሞክራሲ ተቋማት ትኩረት ሰጥቶ መስራቱንም ገልጸዋል።
በዚህም ተቋማት በራሳቸው አዋጅ እንዲተዳደሩ፣ ሥራቸውን ነፃና ገለልተኛ ሆነው ማከናወን እንዲችሉ በማድረግ ለዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ሚናውን ተወጥቷል ብለዋል፡፡
ሕዝቡ ለሚያጋጥሙት የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አቤቱታዎችን በማቅረብ ችግሩ እንዲፈታለት ማድረግ እንደሚችል አስታውቀዋል።
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መንግስትና ሕዝብ የሚገባቸውን አገልግሎትእንዲያገኙ የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሕዝቡ የተቋሙን ኃላፊነት በውል ተገንዝቦ ሊገለገልበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡