ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበበባ፤የካቲት 25/2017(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ፈርመዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ ተቋማት የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ጨምሮ ተያያዥ ጉዳዮችን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ውጤታማ ተግባራት ለማከናወን ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ በሁለቱ ተቋማት መካከል የሚሰሩ ስራዎች ለሀገር ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለስልጣኑ የሚያከናውናቸውን የአካባቢ ጥበቃ ተግባራት ዩኒቨርሲቲው እውቀትን መሠረት ያደረገ የፖሊሲ ግብዓቶችን ለማቅረብ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የአመራሮችንና ፈጻሚዎችን አቅም ለማሳደግ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረጉ ድርድሮችና ውይይቶች ሳይንሳዊ ምክረ ሐሳቦችን ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ ውጤታማ እንዲሆንም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው፥ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥናት ምርምር ዘርፍ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሀገር የተፈረሙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በውጤታማነት ተግባራዊ ለማድረግ ለሚያስፈልጉ ሳይንሳዊ ምርምሮች ከዩኒቨርሲቲው ጋር ለመሥራት መግባባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለስልጣኑ እያዘጋጀ ለሚገኘው የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ ዩኒቨርሲቲው እገዛዎችን እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም