ማዕከሉ በተፋሰሱ ሀገራት ውጤታማ የግድብ ደህንነት ስራዎች ለማከናወን ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ በተፋሰሱ ሀገራት ውጤታማ የግድብ ደህንነት ስራዎች ለማከናወን ያስችላል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2017(ኢዜአ)፡- የናይል ተፋሰስ የግድብ ደህንነት ማዕከል በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ውጤታማ የግድብ ደህንነት ስራዎች ለማከናወን ምቹ አጋጣሚን እንደሚፈጥር የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂኔር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
በናይል ተፋሰስ የግድብ ደህንነት ማዕከል ማቋቋም በሚቻልባቸው ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ምክክር ትናንት በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂኔር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ባለፉት ዓመታት የግድብ ደህንነት የስልጠና ማዕከል ለማቋቋም የተደረገው ጥረት በውሃ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ውሳኔ ላይ መደረሱንና ጥረቱ ፍሬ ማፍራቱን ገልጸዋል።
በናይል ተፋሰስ ሀገራት ውጤታማ የግድብ ደህንነት ስራዎች ለማከናወን የስልጠና ማዕከል ስትራቴጅ ላይ መወያየት ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።
የናይል ቤዝን ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎረንስ ግሬስ (ዶ/ር) ቀጣናዊ ትብብርን በማጎልበት በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እና በተፋሰሱ ዙሪያ ለሚገጥመው የአየር ንብረት ለውጥ የግድብ ደህንነት አስተዳደርን ማቋቋም እንደሚገባ ተናግረዋል።
የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን መጎብኘታቸው ሚኒስቴሩ በመረጃው አስታውሷል።