የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2017(ኢዜአ)፦ የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት እድል በመጠቀም በዘርፉ ያላቸውን የተሳትፎ መጠን እንዲያሳድጉ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ ጥሪ አቀረቡ።
በቶኪዮ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እና ንግድ ዕድሎችና ባህል ማስተዋወቂያ መድረክ ተካሄዷል።
መድረኩን ያዘጋጁት በቶኪዮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የእስያ-አፍሪካ-አረብ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍ (Asia-Africa-Arab 55 Platform) በጋራ በመተባበር ነው።
በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ ኢትዮጵያ እና ጃፓን አንድ ክፍለ ዘመን የሚጠጋ ታሪካዊ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማዕከልና አፍሪካን በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ የምታስተሳስር ትልቅ አቅም ያላት ሀገር ናት ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ በፍጥነት እያደጉ ካሉት የዓለም አገራት ተርታ ያለችና የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አንዷ መሆኗን አመልክተዋል።
በቶኪዮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የጃፓን ኩባንያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።
“Toppan Gravity” እና “Toyo Sola” ኩባንያን በማስተዋወቂያ ስራ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስክ መሰማራታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት አምባሳደሩ።
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) በመድረኩ ላይ የአገራችንን የኢንቨስትመንት ዕድሎች በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው የጃፓን ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱም ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ የጃፓን ባለሃብቶች ስለ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አቅምና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሁኔታ እንዲገነዘቡ ማድረግ መቻሉም ተመላክቷል።
የእስያ-አፍሪካ-አረብ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍ (Asia-Africa-Arab 55 Platform) ሊቀመንበር ሂሳፉሚ ኮጋ በበኩላቸው የጃፓን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
በጃፓን ባለሀብቶች እና የመንግስት ተወካዮች መካከል የመረጃ ልውውጥ (Business to Government) ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የጃፓን ኩባንያዎች፣ የጃፓን መንግስት ተወካዮች፣ የእስያ አፍሪካና አረብ አገራት አምባሳደሮችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸውን በቶኪዮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።