ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና አርጀንቲና በአቪዬሽን ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያና አርጀንቲና በአቪዬሽን ዘርፍ ትብብራቸውን የበለጠ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በኢትዮጵያ የአርጀንቲና አምባሳደር ዡዋን ኢግናቺዮ ሮካታግሊያታ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንን ጎብኝተዋል።

አምባሳደሩ ከባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ ጋር ተወያይተዋል።

ከአንድ ወር በፊት በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ በተካሄደ ድርድር በአጭር ፊርማ ደረጃ የተጠናቀቀውን የአየር አገልግሎት ስምምነት በሙሉ ፊርማ ደረጃ የሚጠናቀቅበት ሂደት ማፋጠን ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።

በአርጀንቲና በአውሮፕላን ማምረት፣ ጥገና፣ ምህንድስና የተሰማራው “FAdeA” ከተሰኘ ኩባንያ ጋር በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ አፍሪካን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አዲስ አበባ ላይ ቅርንጫፍ በሚከፍትበት ሁኔታ እና ለባለስልጣኑ ድጋፍ በሚያደርግበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

በዓለም አቀፋ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያም ተነጋግረዋል።

በአጭር ፊርማ ደረጃ ያለው የአየር አገልግሎት ስምምነት በሙሉ ፊርማ ደረጃ እንዲጠናቀቅ ሁለቱም ወገኞች የበኩላቸውን ጥረት ለማድረግ ተስማምተዋል።

“FAdeA” የተባለው የአርጀንቲና አውሮፕላን አምራችና የጥገና ኩባንያ በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ የሚከፍትበትን ሁኔታ ለመወሰን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የውይይት መድረክ እንዲመቻች መግባባት ላይ መደረሱን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም