ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ የ21ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል  

አዲስ አበባ፤ የካቲት 25/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

በሊጉ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ25 ነጥብ 9ኛ፣ ኢትዮጵያ ቡና በ29 ነጥብ 4ኛ ደረጃን ላይ ይገኛሉ። 

ቡድኖቹ በሊጉ የመጀመሪያ ዙር የሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተገናኝተው ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከሀድያ ሆሳዕና ይጫወታሉ።

ሲዳማ ቡና በ24 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። ሀድያ ሆሳዕና በ31 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሀድያ ሆሳዕና ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በጊዜያዊነት ወደ አንድ ዝቅ ያደርጋል።

ሲዳማ ቡና ድል ከቀናው ከሁለት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ይመለሳል። 

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር በ10ኛ ሳምንት ባደረጉት ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና 3 ለ 2 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። 
 
መርሐ ግብሩ ነገም ቀጥሎ ሲውል ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 

ስሑል ሽሬ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣  መቀሌ 70 እንደርታ ከሃዋሳ ከተማ እና  አዳማ ከአርባምንጭ ከተማ ይጫወታሉ።

የ21ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል። 

የደረጃ ሰንጠረዡን ኢትዮጵያ መድን በ35 ነጥብ እየመራ ነው። ሀዲያ ሆሳዕና በ31 ነጥብ ይከተላል።

ባህር ዳር ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 29 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከሶስተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

አዳማ ከተማ፣ሃዋሳ ከተማ፣ ስሑል ሽሬ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ15ኛ እስከ 18ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ በስምንት ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ነው። 

የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ እና የአርባምንጭ ከተማው አህመድ ሁሴን በተመሳሳይ ሰባት ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም