የዱር እንስሳት ጥበቃ ፖሊሲ ለውጥ መደረጉ የግሉ ዘርፍ በቱሪዝም እንዲሳተፍ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የዱር እንስሳት ጥበቃ ፖሊሲ ለውጥ መደረጉ የግሉ ዘርፍ በቱሪዝም እንዲሳተፍ ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2017(ኢዜአ)፦ የዱር እንስሳት ጥበቃ ፖሊሲ ለውጥ መደረጉ የግሉ ዘርፍ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ልማት የሚያደርገውን ተሳትፎ ይበልጥ እንደሚያጠናክረው የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
ዛሬ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቀንን ምክንያት በማድረግ በጉለሌ እጽዋት ማዕከል ጉብኝት ተደርጓል፡፡
በጉብኝቱ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ(ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) ከጉብኝቱ በኋላ፤ ኢትዮጵያ የበርካታ የዱር እንስሳት ባለቤት ብትሆንም ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ባለመቻሉ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ አይደለችም ብለዋል፡፡
ከባለፉት የለውጥ አመታት ወዲህ ግን መንግስት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመሰጠት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲያስገኝ በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከተሰሩ ስራዎች መካከል የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴዔታው፤ ይህም መንግስት ብቻውን ይሰራ የነበረውን ዘርፍ የግል በለሃብቱ እንዲሳተፍበት አድርጓል ብለዋል፡፡
መንግስት እና የግሉ ዘርፍ በጋራ የዱር እንስሳት ሃብትን በመጠበቅ ዘርፉ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን አስችሏል ነው ያሉት፡፡
የፌደራል መንግስት ከሚሰራው የዱር እንስሳት ጥበቃ በተጨማሪ ክልሎች በራሳቸው አቅም ለዱር እንስሳት የሚሆኑ ፓርኮችን የማዘጋጀት ተግባር እንዲያከናውኑ እድል መፍጠሩን አንስተዋል።
በቀጣይ አሁን ካላው በተሻለ ሁኔታ የዱር እንስሳት ሃብትን ወደ ላቀ የቱሪዝም መዳረሻ አማራጭነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር የዱር እንስሳት የጥበቃ ሽፋንን ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በፈረንጆች የዘመን ቀመር በ2030 የምድሪቱን የዱር እንስሳት የጥበቃ ቦታ ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዱር እንስሳት ጥበቃ የሚሆን የዓለም የደን ጥበቃ ቦታ ሽፋን በአማካኝ 17 በመቶ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ደግሞ 14 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የኢትዮጵያን የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታ የደን ሽፋን ከፍ በማድረግ ለዓለም የዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታ ሽፋን የበኩላችንን ለመወጣት በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የዱር እንስሳት ቀን "ፋይናንስ ለዱር ህይወት ጥበቃ፣ ለሠዎችና ለፕላኔታች ደህንነት" በሚል መሪ ሃሳብ ታስቦ ውሏል።