ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች እንዲጸኑ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች እንዲጸኑ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች እንዲፀኑ በሰው ኃይል ማፍራትና በጥናትና ምርምር ስራዎች የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገለፀ።
ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ለመሆን የጀመራቸውን ስራዎች ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ አዳዲስ አሰራሮችን መዘርጋቱንም ገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ራሄል አርጋው (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው ዘመኑ የሚጠይቀውን ብዙ የሰው ኃይል የማፍራት ተልዕኮውን ለመወጣት አዳዲስ ስልቶችን ነድፎ እየተገበረ ነው።
የራስ ገዝነት ሽግግር ላይ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ረገድ ተልዕኮውን በጥራት ለመከወን የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም አንስተዋል።
የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ፣ ገበያ የሚፈልጋቸውን የትምህርት መስኮችን የማካተት፣ የመምህራንን አቅም የማሳደግና ምቹ የስራ አካባቢን ከመፍጠር አኳያ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
ተማሪዎች ቴክኖሎጂን ያማከለ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ከኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ።
በተለያዩ ዘርፎች የዲጂታል አማራጮችን ለማስፋት ዘመናዊ ትምህርት ክፍሎችን እየተደራጁ መሆኑን ገልጸው፤ የቴክኖሎጂ ምርምር ኢንስቲትዩት ለማቋቋም በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች እንዲጸኑ የተማረ የሰው ሃይል ከማፍራት ባለፈ ምሁራን በጥናትና ምርምር የታገዙ ገንቢ ምክረ-ሀሳቦችን እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ምሁራን አገር በቀል የመፍትሄ ሀሳቦችን በመስጠትና ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ የማማከር አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም እንዲሁ።