የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን የድንበር ንግድ የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን የድንበር ንግድ የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፤የካቲት 24/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የድንበር ንግድ የጋራ ኮሚቴ የመጀመሪያ ስብሰባውን በቢሾፍቱ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የንግድ ትስስርና የወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ውሃብረቢ እንደገለፁት፥ በስብሰባው ሁለቱ ሀገራት የተፈራረሙት የድንበር ንግድ ፕሮቶኮል አፈፃፀም ያለበትን ደረጃ እንደሚገመገም ገልጸዋል።
በቀጣይ ስምምነቱን በመተግበር የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እንደሚደረግ አመልክተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በየካቲት ወር 2017 ዓ.ም የድንበር ንግድ ፕሮቶኮል መፈራረማቸውን አውስተዋል።
ስምምነቱ በድንበር አካባቢ ለሚኖሩ ለሁለቱም ህዝቦች መሰረታዊ የሆኑ የንግድ እቃዎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የሁለቱ ሀገራት ህዝቦችን በኢኮኖሚ በማስተሳሰር እንዲሁም በድንበር አካባቢ ሠላምና መረጋጋትን በመፍጠር በኩል ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ነው የገለጹት።
የጋራ ውይይትንና ትብብርን የሚጠይቁ እንዲሁም የድንበር ንግድ ፕሮቶኮል ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ እንደ ኮንትሮባንድ፣ህገ ወጥ ንግድ እና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ጥቅም ለደቡብ ሱዳን ጥቅም ነው፤ የደቡብ ሱዳን ጥቅም የኢትዮጵያም ጥቅም ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ ለጋራ ጥቅም በትብብር በጋራ መስራት እንደሚገባ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።