ጄትሮ የኢትዮጵያ እና የጃፓን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ጄትሮ የኢትዮጵያ እና የጃፓን የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ
አዲስ አበባ፤የካቲት 24/2017(ኢዜአ)፡-የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት (JETRO) የኢትዮጵያ እና የጃፓን የኢንቨስትመንት ትብብር ለማጎልበት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ከድርጅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ካዙያ ናካጆ ጋር በቶኪዮ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ ተገኝተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት እድሎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ ድርጅቱ የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።
አምባሳደር ዳባ ጄትሮ የአዲስ አበባ ቢሮውን የስራ እንቅስቃሴ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
ተቋሙ እ.አ.አ ኦገስት ወር 2025 በጃፓን ዮካሃማ በሚካሄደው ዘጠነኛ የጃፓን አፍሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፎረም(ቲካድ) ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትና ቢዝነስ ዕድሎች የሚያስተዋውቅ መድረክ እንዲያዘጋጅ ጠይቀዋል።
የጄትሮ ድርጅት ምክትል ፕሬዝዳንት ካዙያ ናካጆ ድርጅቱ የኢትዮጵያን የኢንስትመንት ዕድሎች ለጃፓን ባለሀብቶች የማስተዋወቅ ስራ እንደሚያከናውን መግለጻቸውን በቶኪዮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
እ.አ.አ በ1952 የተቋቋመው የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት (JETRO) የጃፓን እና የሌሎች ሀገራት የኢንቨስትመንት እና የንግድ ትብብር የማጠናከር ስራ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።