ቀጥታ፡

ተቋማትና ባለሃብቶች የሚያደርጉት የማዕድ ማጋራት በጎ ስራ በፆም ወራትም ተጠናክሮ ቀጥሏል - ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬዳዋ፤ የካቲት 23/2017(ኢዜአ)፡- የአስተዳደሩ ተቋማትና ባለሃብቶች የሚያደርጉት የማዕድ ማጋራት በጎ ስራ በፆም ወራትም ተጠናክሮ መቀጠሉን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

የድሬዳዋ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና አንድ በአሜሪካ የሚኖሩ ባለሃብት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የተገዙ ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ቁሶችን ዛሬ ድጋፍ ለሚሹ ቤተሰቦች ድጋፍ አድርገዋል።

ኮሚሽኑ ስምንት ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ የገዛቸውን የምግብ ቁሶች ለ1ሺህ 150 የአስተዳደሩ ቤተሰቦች አከፋፍሏል።


 

ከተደረጉት ድጋፎች መካከል የምግብ ዘይት፣ ዱቄት፣ ወተት፣ ቴምር፣ ቱና፣ ጁስ እና ሌሎች የምግብ አይነቶች ይገኙበታል።

በተጨማሪም አንድ በአሜሪካ የሚኖሩ ባለሃብት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የተገዙ የምግብ ቁሶችን በተወካዮቻቸው በኩል በአስተዳደሩ ለሚገኙ 300 ድጋፍ የሚሹ ቤተሰቦች አጋርተዋል።

በማዕድ ማጋራት ስነስርአቱ ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር እና የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ድጋፉን ተቀብለው ለቤተሰቦቹ አከፋፍለዋል።


 

በዚሁ ወቅት ከንቲባ ከድር የረመዳን እና የአብይ አፅዋማትን ምክንያት በማድረግ ድጋፍ ለሚሹ ቤተሰቦች ማዕድ የማጋራቱ በጎ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የመተባበርና የመደጋገፍ ባህልን በመጠበቅ በበጎ ስራ ላይ መሳተፍ የሁሉም ባለሃብቶች፣ ተቋማትና ነዋሪዎች የህሊና ኃላፊነት መሆኑን በማሳሰብ።

በብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ሰው ተኮር አሻጋሪ ልማቶችንና በጎ ተግባራትን ማከናወኑን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ለአደጋ ስጋት የማይበገር ማህበረሰብ ከመገንባት ጎን ለጎን ድጋፍ የሚሹ ነዋሪዎችን ችግር ለማቃለል በትጋት እየሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአስተዳደሩ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ሱሌይማን ዓሊ ናቸው።

በስምንት ሚሊዮን ብር የተገዙና ለችግረኛ ቤተሰቦች የተሰጡት የምግብ ሸቀጦች የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆናቸውን በመግለፅ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም