ትውልዱ በሁሉም መስክ የተሻለች ኢትዮጵያን በመገንባት የራሱን ድል ማስመዝገብ አለበት - ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ በሁሉም መስክ የተሻለች ኢትዮጵያን በመገንባት የራሱን ድል ማስመዝገብ አለበት - ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን
አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2017(ኢዜአ)፡- ትውልዱ ከዓድዋ ጀግኖች የተረከባትን ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ የተሻለች በማድረግ የራሱን ድል ማስመዝገብ እንዳለበት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ገለፁ።
129ኛው የዓድዋ ድል በዓል "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።
የጥንታዊት የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዓድዋ ጀግኖች የውስጥ ችግሮቻቸውን ወደ ጎን ብለው በአንድነት በመቆም የውጭ ወራሪ ሃይልን በማሸነፍ ሀገራቸውን ማስከበራቸውን አውስተዋል።
የዛሬ 129 ዓመት ኢትዮጵያ አሸናፊነቷን፣ አይበገሬነቷን፣ ድል አድራጊነቷን በደማቁ ፅፋለች ነው ያሉት።
የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያውያን ባለፈ መላው ጥቁር ህዝቦች የሚኮሩበት የቅኝ ገዥዎችን ቅስም የሰበረ ታላቅ ድል መሆኑን ተናግረዋል።
የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ ድል ተባብሮ መስራትን በመማር የልማትና የሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ በንቃት መረባረብና የራሱን ድል ማስመዝገብ አለበት ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ጠላቶች አንድነታችንን ለመሸርሸርና ሀገራችንን ለማዳከም እንደሚሞክሩ በማንሳት፤ ትውልዱ የጠላትን ሴራ በማክሸፍ ጠንካራና የበለጸገች ሀገርን ገንብቶ ለተተኪው እንዲያስረክብ አደራ ብለዋል።
በበዓሉ ላይ ድሉን በሚመለከት ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው የዓድዋ ድል የ19ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ጦርነት እና ድል ነው ብለዋል።
የድሉ ሚስጥር ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ክብር ለማስጠበቅ ያሳዩት ፍጹም አንድነትና ሕብረት መሆኑንም ተናግረዋል።
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያስከበረና የአሸናፊነት ስነ-ልቦናን ያጎናጸፈ ድል እንደሆነም ገልጸዋል።
ለአፍሪካውያን የአርነት ትግልና የፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ መፋፋም አርዓያ የሆነ ድል ነው ብለዋል።
የዓድዋ ድል ለጥቁር ሕዝቦች የእኩልነት ጥያቄ እንደ ፋና ዋጊ የሚወሰድ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ትውልዱ የዓድዋ ድል ነጻነት እንዲሁ የተገኘ ሳይሆን ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት፣ የአንድነት ውጤት መሆኑን መማር እንደሚገባውም ተናግረዋል።
ለጠላት ተላላኪ ባንዳ አለመሆንን ከዓድዋ ድል ጀግኖች መውረስ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለሀገር ክብር መስጠትን ከድሉ መማር እንደሚገባ ጠቁመው ለሰንደቅ ዓላማ፣ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለህገ መንግሥት እና ለብሔራዊ ጥቅም መከበር መሥራትና ማክበር እንደሚገባም ጠቁመዋል።