ቀጥታ፡

ወጣቱ ወቅቱ የሚፈልገውን እውቀት በመጨበጥ የሀገሩን ዕድገት የሚያረጋግጡ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅበታል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2017(ኢዜአ)፡- ወጣቱ በትምህርት በቂ እውቀት በመጨበጥና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሀገርን ዕድገት በሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ መረባረብ እንደሚጠበቅበት በ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል አከባበር ላይ የተሳተፉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

129ኛው የዓድዋ ድል በዓል ''ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል'' በሚል መሪ ሀሳብ በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተከበረው መርሃ-ግብር ላይ የታደሙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉት ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተጋድለው ያስገኙትን ድል የአሁኑ ትውልድ በሀገር ልማት ሊደግመው ይገባል።

የአሁኑ ትውልድ ዘመኑ የሚፈልገውን እውቀት በትምህርት በመገብየት ለመጪው ትውልድ ካደጉት ሀገራት ተርታ የተሰለፈች ሀገርን ለማስረከብ መስራት አለበት ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባል ሻለቃ ሳሙኤል ለገሰ እንዳሉት ወጣቱ ዘመኑ የሚፈልገውን ቴክኖሎጂ በአግባቡ በመጠቀም ለሀገር ልማት ለማዋል ለትምህርት ልዩ ትኩረት መስጠት ይጠበቅበታል።

ከዛሬ 129 ዓመታት በፊት በኋላቀር መሳሪያ በቴክኖሎጂ የታገዘውን የወራሪውን ሃይል ድል ማድረግ የተቻለው በጀግኖች አባቶችና እናቶች የአሸናፊነት ጽናት ነው ብለዋል።

ትውልዱ ከአባቶቹ ሊማራቸው የሚገቡ በርካታ የጽናትና የአሸናፊነት ጥንካሬ መኖሩን ጠቅሰው፣ በተለይም ድህነትን ለማሸነፍ በሚደረገው ጥረት ንቁ ተሳታፊ መሆን አለበት ያለው ደግሞ በበዓሉ ላይ የታደመው ወጣት ሰለሞን ሃብቴ ነው።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባል ሸዋንግዛው ጸደቀ በበኩላቸው የአሁኑ ትውልድ ጠንክሮ በመስራት ማሸነፍ ያለበት ድህነትን መሆኑን ተናግረዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የተሳተፈችው ተማሪ ቬሮኒካ ፍቅሬ በሰጠችው አስተያየት ከዓድዋ ድል ጠንክሮ በመማር ለሀገር እድገት የራሷን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚያስችል ግንዛቤ መጨበጧን ተናግራለች።

ተማሪው በትምህርቱ ሰራተኛው በተሰማራበት የስራ መስክ ጠንክሮ በመስራት በአባቶች ድል አድራጊነት የተረከብናትን ሀገር በሁሉም መስክ ማሳደግ እንደሚገባ የተናገረው የበዓሉ ታዳሚ ተማሪ ዮስቲና ያለው ነው።

ለዚህ ጠንክሮ በመማር በቂ እውቀት መጨበት እንደሚያስፈልግ መረዳታቸውንም ጠቅስዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የነጻነት ተምሳሌት የሆነውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለአሁኑ ትውልድ በክብር አስረክበዋል።

ይህም ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ እየተገነባች መምጣቷን ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም