የሊጉ የዋንጫ ተፎካካሪዎች የሚያደርጓቸው ተጠባቂ ጨዋታዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ የዋንጫ ተፎካካሪዎች የሚያደርጓቸው ተጠባቂ ጨዋታዎች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 23/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል።
ድሬዳዋ ከተማ ከመቻል ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በሊጉ ድሬዳዋ ከተማ በ20 ነጥብ 14ኛ፣ መቻል በ27 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
መቻል ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ዝቅ ያደርጋል።
በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማ ድል ከቀናው ከወራጅ ቀጠና አካባቢ በመጠኑም ቢሆን የመራቅ እድል ያገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።
የ20ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ምሽት 12 ላይ ባህር ዳር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገናኛል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ29 ነጥብ 3ኛ ደረጃን ይዟል። ባህር ዳር ከተማ በ26 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን ካሸነፈ በ32 ነጥብ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ያደርጋል። ይህም ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ዝቅ ያደገዋል።
በአንጻሩ ለባህር ዳር ከተማ መርሃ ግብሩ ወደ ዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ለመጠጋት መልካም አጋጣሚን ይፈጥርለታል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።
በተያያዘም ትናንት በ20ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ በተደረጉ ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ የሊጉ መሪን ኢትዮጵያ መድንን፣ አርባምንጭ ከተማ ፋሲል ከነማን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፈዋል።