ቀጥታ፡

በክልሉ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል

ሆሳዕና ፤የካቲት 23/2017(ኢዜአ) :-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።

"ውጤታማ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ትግበራ ለብልፅግናችን!" በሚል መሪ ሃሳብ በክልሉ ጤና ቢሮ መካሄድ በጀመረው መርሃ ግብር የቢሮው ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ ለኢዜአ እንዳሉት፥ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ የጀርባ አጥንት ነው።

በክልሉ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

መድረኩም ባለፉት ዓመታት በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የተገኙ ስኬቶችን ማስቀጠልና የተስተዋሉ ክፍተቶችን ማረምን ዓላማ ያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

እንደ ሀገርም ሆነ ክልል ተቀርጾ እየተተገበረ ያለው በሽታን መካከል መሰረት ላደረገው የጤና ፖሊሲ ስኬት የሚረዳ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ተነድፎ በክልሉ በሙከራ ደረጃ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል፡፡

በክልሉ በዚህ ወቅት ከ1 ሺህ 100 በላይ የጤና ኬላዎች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

ከ2 ሺህ 500 በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተመድበው በሽታን በመከላከልና በማከም ተግባር ላይ እንደሚገኙም ነው ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በተሟላ መንገድ ወደ ትግበራ ገብቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ የተቻለበት ነው ብለዋል፡፡

በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን ስኬት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሁለተኛው ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማሻሻያ እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡን ተከትሎ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ደረጃ ማሻሻል መቻሉንም አብራርተዋል፡፡

የእናቶችና ህፃናትን ሞት ከመቀነስ፣ የአካባቢን ጤና ከመጠበቅና የቲቢ በሽታን ከመከላከል አኳያ ስኬቶች እየተመዘገቡ ቢሆንም በዚህ ወቅት በተለያየ ምክንያት የተስተዋለውን መቀዛቀዝ ለማጠናከር መድረኩ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ፌስቲቫሉ ለተከታታይ ሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በፕሮግራሙ ትግበራና በማሻሻያ ሰነድ ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም