ቀጥታ፡

ጀግኖች አባቶቻችን በዓድዋ ድል ያሳዩትን የሀገር ፍቅርና አንድነት፤ ትውልዱ ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ ማስቀጠል አለበት

ጋምቤላ፤የካቲት 23/2017(ኢዜአ)፦ጀግኖች አባቶቻችን በዓድዋ ድል ያሳዩትን የሀገር ፍቅርና አንድነት በማስቀጠል ዘላቂ ሰላምና ልማትን የማረጋገጡ ተግባር የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው ሲሉ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሏክ ሮን (ዶ/ር) ገለፁ።

129ኛው የዓድዋ ድል በዓል በክልል ደረጃ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በበዓሉ የታደሙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሰተዳድር ጋትሏክ ሮን(ዶ/ር) የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች የጀግነትና የአንድነት ተጋድሎ ብሔራዊ ዓርማ ነው ብለዋል።

ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ጦርነት በተባበረ ክንዳቸውና በአይበገሬ ወኔያቸው ወራሪውን ኃይል በማንበርከክ የሀገራቸውን ክብር ከፍ አድርገው ለዓለም ህዝቦች ያሳዩበት የድል በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በዘመኑ ተንሰራፍቶ የነበረውን አፍሪካን የመቀራመት አጀንዳ በሃይል መስበር እንደሚቻል ያሳዩበት አንፀባራቂ የድል ታሪክ መሆኑንም ገልጸዋል።

በብዝሃነት ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር በዓድዋ ድል የታየውን አንድነትና አብሮት በመጠበቅ የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ልማት የማረጋገጡ ሂደት የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው ሲሉም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጁል ናንጋል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የዓድዋ ድል ለጥቁር ህዝቦች የድል ብስራት ችቦ ሆኖ ለትውልድ እየተላለፈ የሚገኝ የድል ሃውልታችን ነው።

የዓድዋ ድል ጀግኖች አባቶቻችን በአንድነት ቆመው ወራሪውን ኃይል አሳፍረው በመመለስ የሀገርን ክብር ያፀኑበት ታላቅ ክብረ በዓል እንደሆነም ተናግረዋል።

በመሆኑም ዓድዋን ስናከብር በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነትና አብሮነት በማጠናከር ለአገራችን ሁለንተናዊ ብልፅግና በጋራ ልንተጋ ይገባል ብለዋል።

በክልል ደረጃ በጋምቤላ ከተማ በተከበረው 129ኛው የአድዋ ድል በዓል ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልል የፀጥታ አካላት ወታደራዊ የሰልፍ ትርኢት ያሳዩ ሲሆን፤ በዓሉን የሚዘክሩ የተለያዩ ስነ-ጽሁፎችም ቀርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም